የጋቦን 2017 ተሳታፊዎች ፕሮፋይል | አልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን [የበረሃ ቀበሮዎቹ]

አልጄሪያ ካላት የቡድን ስብስብ ጥራት አንፃር ለአፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮንነት ከሚገመቱት ሃገራት መካከል ነች፡፡

በአለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ማጣሪያ አልጄሪያ ባስመዘገበችው ውጤት ምክንያት ሚሎቫን ራይቫክን አሰናብታ ጆርጀስ ሊክንስ ሾማለች፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫ ድል ማጣጣም ከቻሉ ዓመታት የተቆጠሩት የበረሃ ቀበሮዎች በ2016 መጨረሻ ወራት ያሳዩት የወረደ አቋምን ለማስተካከል ወደ ጋቦን አቅንተዋል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 16

ውጤት፡ አንድ ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮን (1990)

አሰልጣኝ፡ ጆርጀስ ሊክንስ

አልጄሪያ በምድብ ሁለት ከጠንካሮቹ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ እና ዝቅተኛ ግምት ከተሰጣት ዚምባቡዌ ጋር ተደልድላለች፡፡ ጋናን በ2010 የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ያደረሱት አሰልጣኝ ሚሎቫን ራይቫክ በተጫዋቾች ጥያቄ መሰረት ከአሰልጣኝነታቸው ተሰናብተው ቱኒዚያን ከዚህ ቀደም ያሰለጠኑት ጆርጀስ ሊክንስ አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡ ሊክንስ ብሄራዊ ቡድኑ ከገባበት የውጤት ቀውስ ለማዳን የግድ እንደገና ቡድኑን መስራት አለባቸው፡፡ ለዚህም ይመስላል ለረጅም ግዜ በአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን የምናውቃቸው ሶፊያን ፊጉሊ እና ካርል ሜጃኒን የቀነሱት፡፡ አልጄሪያ የአጥቂ መስመሩ ጠንካራ ቢሆንም የተከላካይ ስፍራው ደግሞ በንፅፅር የደከመ ነው፡፡ በግል ብቃታቸው የተወደሱ ተጫዋቾችን ያሰባሰበው ቡድኑ ኳስን መሰራት አድርጎ ከመጫወቱ ባሻገር የፊት መስመሩ እጅግ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ የኃላ መስመሩ ክሪስቲያን ጎርከፍ ከስራቸው በፈቃዳቸው ከለቀቁ ወዲያ እየወረደ መጥቷል፡፡ በተለይ በምድቡ ሴኔጋል እና ቱኒዚያ ስለሚገኙ ሊክንስ የተጠናከ የተከላካይ ስፍራ ከሌላቸው የምድብ የማለፍ ነገር ያከትምለታል፡፡

ተቀማጭነቱን በኦትዋ ካናዳ ያደረገው አልጄሪያዊው የእግርኳስ ጋዜጠኛ ዋሊድ ባይልካ ስለሃገሩ የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋ፣ ስጋቶች እና ተያያዝዥ ጉዳዮች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ዋሊድ የdzfoot.com ፀሃፊ ሲሆን በአፍሪካ እግርኳስ ላይ ስለሚያውጠነጥነው Mesfouf Koshary ፖድካስትም አዘጋጅ ነው፡፡

ስለምድብ ሁለት

“ከፊፋ የሃገራት ደረጃ አንፃር አንፃር ከተመለከትነው በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ከባዱ ምድብ ይህ ነው፡፡ ከምድቡ ሶስት ቡድኖች ውስጥ ሶስቱ በአፍሪካ የሃገራት ደረጃ የመጀመሪያዎቹ 5 ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ይህ ሴኔጋልን ያጠቃልላል የምድቡ ትልቅ ቡድን ናት፡፡ ምድቡ ቀላል አይሆንም፡፡ አልጄሪያ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የግድ ጣጣዋን ከሴኔጋል ጨዋታ በፊት (የመጨረሻው የምድብ ጨዋታ) በፊት ማድረግ አለባት፡፡ ምክንያቱም ይህ ጨዋታ ቀላል ስላልሆነ፡፡ ዚምባቡዌም ቀላል ግምት የሚሰጣት አይደለችም፡፡ አቅማቸውን እና ምን መሰራት እንደሚችሉ ከካሜሮን ጋር ባደረጉት የአቋም መለኪያ ጨዋታ አይተናል፡፡”

የዋንጫ ተስፋ

“አልጄሪያ ብዙ የማጥቃት አማራጮች ቢኖሯትም የመሃል እና የኃላ ክፍሉ ላይ የሚነሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጠንካራ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን እነዚህ ማጤንን ያስፈልጋል፡፡ ቡድኑ ሩብ ፍፃሜ ወይንም ግማሽ ፍፃሜ እንደሚደርስ እገምታለሁ፡፡ ዋንጫ ማንሳት ግን እኔ እንደማስበው ይከብዳል፡፡”

ከሃገር ውስጥ ሊግ የተመረጡ ተጫዋቾች

“ከተመረጡት መካከል ሶስቱ ቢሆኑ ነው በቋሚ አሰላለፉ ውስጥ የመግባት እድል ያላቸው፡፡ ሊክንስ የጠራቸው ሁለቱም የቀኝ መስመር ተከላካዮች ቤልከሂተር እና ሚፍታህ በአልጄሪያ ነው የሚጫወቱት፡፡ ስለዚህም አንዳቸው ቋሚ የመሆን እድል አላቸው፡፡ ቤልከሂተር በተለየ ከሞሪታንያ ጋር ቅዳሜ በተደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ጥሩ ነበር፡፡ ግብ ጠባቂው ማሊክ አሴላከ ከረይስ ምቡሁሊ ቀድሞ የአልጄሪያን ግብ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡ ሌሎቹ ተጫዋቾች ራህማኒ እና ቤንያህያ ለደቂቃዎች የሚጫወቱ አይመስለኝም፡፡”

ስጋት

“የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ቡድናችን ክፉኛ ጎድተዋል፡፡ አሁን ላይ አዲስ አሰልጣኝ አለን ግን በአለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድቡ መጨረሸኛ ነን፡፡ ይህ ደግሞ ቡድኑን ለውጦቷል፡፡ ቋሚ የነበሩ በርካታ ተጫዋቾችን ከቡድኑ አስወጥቷል ልክእንደ ሶፊያን ፊጉሁሊ፣ ካርል ሜጃኒ፣ መህዲ ዚፋን፣ ያሲን ቤንዚያ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ቡድን ዳግም እየተሰራ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ፌድሬሽኑም ደጋፊዎችም ያውቃሉ፡፡”

ልንመለከታቸው የሚገቡ ተጫዋቾች

“ብዙዎች ኢስላም ስሊማኒ፣ ያሲን ብራሂም፣ ሪያድ ማህሬዝ እና ነቢል ቤንታሊብን የመሳሰሉ ትልልቅ ስሞችን ያውቃሉ፡፡ እኔ ግን አይኔን ወደ ዳይናሞ ዛግሬቡ የመስመር ተጫዋች ኤል አረብ ሂላል ሱዳኒ ተክያለው፡፡ ከቡድኑ ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻ 10 ጨዋታዎች 9 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ሌላው የ21 ዓመቱ የመሃል ተከላካይ ራሚ ቤንሰባይኒ ነው፡፡ ራሚ የተሳካ ውድድር እንደሚያሳልፍ እጠብቃለው፡፡”

ሪያድ ማህሬዝ ዓመቱን በአፍሪካ እግርኳስ ላይ ነግሷል፡፡ አልጄሪያ ከማህሬዝ ከፍተኛ ግልጋሎትን እንደምትጠብቅ የታወቀ ነው፡፡ የናፖሊው ግራ ተመላላሽ ፋውዚ ጉልሃም በማጥቃቱ በኩል የተዋጣለት ቢሆንም መከላከሉ ላይ ይበልጥ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ቡድኑ ያሉበትን የመከላከል ችግሮች ከቀረፈ ከምድቡ ማለፍ የማይችልበት አንድም ምክንያት የለም፡፡

የማጣሪያ ጉዞ

አልጄሪያ በምድብ 10 ከኢትዮጵያ፣ ሌሶቶ እና ሲሸልስ ጋር ተደልድላ በመሪነተ ጨርሰለች፡፡ አዲስ አበባ ላይ 3-3 ከተለያየችበት የአቻ ውጤት በስተቀር ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ችላለች፡፡ 25 ግቦችን በስድስት ጨዋታ ስታስቆጥር የተቆጠረባት የግብ መጠን አምስት ነው፡፡ ከአምስቱ መካከል አራቱ በኢትዮጵያ ነው የተቆጠረባት፡፡ አልጄሪያ በተለይ በሜዳዋ የግብ ናዳ እያወረደች ማሸነፍ ችላለች፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ሸምሰዲን ራህማኒ (ኤምኦ ቤጃያ/አልጄሪያ)፣ ሪየስ ምቦህሊ (አንታሊያስፖር/ቱርክ)፣ ማሊክ አሴላ (ጂኤስኬ ካቤሌ/አልጄሪያ)

ተከላካዮች

አይሳ ማንዲ (ሪያል ቤቲስ/ስፔን)፣ ፋውዚ ጉልሃም (ናፖሊ/ጣሊያን)፣ ሊያሲን ካዶሞሮ (ኤስ. ጄኔቭ/ስዊዘርላንድ)፣ ሃኪም ቤልከሩይ(ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ/ቱኒዚያ)፣ጀማል ሜስባህ (ክሮቶኔ/ጣሊያን)፣ መሃመድ ቤንያህያ (ዩኤስኤም አርጀር/አልጄሪያ)፣ ሞክታር ቤልካትር (ክለብ አፍሪካ/ቱኒዚያ)፣ አምር ቤንሳባኒ (ስታደ ሬን/ፈረንሳይ)፣ መሃመድ ሚፍታህ (ዩኤስኤም አልጀር/አልጄሪያ)

አማካዮች

ኢስማኤል ቤንአስር (አርሰናል)፣ ነቢል ቤንታሊብ (ሻልክ 04/ጀርመን)፣ ያሲን ብራሂሚ (ፖርቶ/ፖርቹጋል)፣ አድሌን ጉዱዮራ (ዋትፎርድ/እንግሊዝ)፣ መህዲ አቢየድ (ዲዮን/ፈረንሳይ)

አጥቂዎች

ኢስላም ስሊማኒ፣ ሪያድ ማህሬዝ (ሁለቱም ከሌስተር ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ሶፊያን ሃኒ (አንደርሌክት/ቤልጂየም)፣ ባግዳድ ቦንጃ (አል ሳድ/ካታር)፣ ኤል አረብ ሂላል ሱዳኒ (ዳይናሞ ዛግሬብ/ክሮሺያ)፣ ራሺድ ገዛሃል (ኦሎምፒክ ሊዮን/ፈረንሳይ)

አልጄሪያ በምድብ ሁለት የመክፈቻ ጨዋታ ዚምባቡዌን ዕሁድ ትገጥማለች፡፡

Leave a Reply