ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 ወላይታ ድቻ ፡ ታክቲካዊ ትንታኔ

በአበበ ቢቂላ ስታድየም የተደረገው የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ግሩም ድባብ ደምቆ በአምናው ቻምፒዮን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ጊዜያዊ አሰልጣኝነቱን የተረከቡት ፋሲል እና ዘሪሁንም የመጀመርያ ጨዋታቸውን በድል አሟሽተዋል፡፡

በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4-3-3 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ወደ ሜዳ ሲገባ ወላይታ ድቻ በበኩሉ በ3-5-2 ፎርሜሽን ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡

(ምስል 1)

 

4—3-3 ከ 3-5-2

ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዘመኑ በተደጋጋሚ የተጠቀመበትን 4-3-3 ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በአማካይ መስመር ላይ ከአማካይ ተከላካዩ ተስፋዬ አለባቸው ግራ እና ቀኝ ምንያህል ተሾመ እና ምንተስኖት አዳነን አሰልፏል፡፡ ሶስቱ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ሲወጡት የነበረው ሚናም የተለያየ ነበር፡፡ ምንተስኖት አዳነ ‹‹ ነፃ ሚና ›› በሚመስል መልኩ በተለይም ማጥቃት ላይ ያተኮረ ሚናን ሲወጣ ምንያህል ተሾመ የጨዋታ አቀናባሪነት ሚና ነበረው፡፡ ምንያህል የቡድኑን የኳስ ስርጭት ሲመራ ፣ በአግድሞሽ እንቅስቃሴ (lateral movement) ከፉልባኩ ዘካርያስ እና የመስመር አጥቂው በኃይሉ ጋር የማጥቃት ማእዘናትን (attacking angles) ሲፈጥርና የመቀባበያ አማራጮችን (passing lane options) ሲያሰፋ ተስተውሏል፡፡ በአማካይ ተከላካይነት የተሰለፈው ተስፋዬ ደግሞ ከተከላካዮች በቅርብ ርቀት በመቆም ለተከላካዮቹ ሽፋን ሲሰጥ ውሏል፡፡ ተስፋዬ በቡድኑ የመከላከልም (defending phase) ሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ (attacking phase) ላይ የነበረው ሚና ተመሳሳይ ነበር፡፡ ለተከላካዮቸ ሽፋን መስጠት፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጠቀመበት 4-3-3 ከወላይታ ድቻ 3-5-2 አንፃር ለመስመር አጥቂዎቹ የመጫወቻ ክፍተት የሰጣቸው ሲሆን በተለይ ድቻዎች በማጥቃት ወቅት የመስመር አማካዮች ጥለው የሚሄዱትን ክፍተት በኃይሉ አሰፋ ከሞላ ጎደል ተጠቅሞበታል፡፡ ሜዳውን ወደጎን በመለጠጥ ሶስቱ የመሃል ተከላካዮች ቅርፃቸው እንዲበታተንም ሲጥር ተስተውሏል፡፡

ወላይታ ድቻ እንደተለመደው በ3-5-2 የጨዋታ አቀራረብ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ ቡድኑ የአማካይ ክፍሉ በ5 ተጫዋቾች የተዋቀረ ሲሆን ከአሸናፊ ሽብሩ ግራ እና ቀኝ የተሰለፉት ዮሴፍ እና ብሩክ በአግድሞሸ እንቅስቃሴ የቅዱስ ጊዮርጊስን እንቅስቃሴ ለመግታት ሞክረዋል፡፡

በአጥቂነት ሚና የገቡት ባዬ እና አላዛር ሚናም የተለያየ ነበር፡፡ ባዬ ወደ ግራ መስመር (የቅዱስ ጊዮርጊስ ደካማ ክፍል) በማዘንበል በፉልበኩ እና ተከላካዩ መካከል (channel) ያለውን ክፍተት ለመጠቀም ሲጥር አላዛር ደግሞ ወደ ኋላ በመመለስ የተደራቢ አጥቂነት ሚናን ሲወጣ ተስተውሏል፡፡

(ምስል 2)

2222

የጊዮርጊስ ወደ ግራ ያመዘነ አጨዋወት

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በድረገፃችን እንደተብራራው የቅዱስ ጊዮርጊስ የግራ መስመር ጠንካራ ጎኑ ነው፡፡ በፉልባኩ ዘካርያስ ቱጂ ፣ ከሶስቱ አማካዮች ወደ ግራ ያመዘነ አማካይ ሆኖ የተሰለፈው ምንያህል ተሾመ እና በግራ ክንፍ አጥቂነት የተሰለፈው በኃይሉ አሰፋ መካከል ያለው መግባባት ጥሩ ሲሆን የድቻ የቀኝ መስመር ደካማ መሆን ተደምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቦታው የበላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በተለይ ከ10ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታውን በቀኝ መስመር የጀመረው በኃይሉ ወደ ግራ መስመር ከተመለሰ በኋላ የማጥቃት ጫና እንዲፈጥሩ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ በኃይሉ በተደጋጋሚ ኳሶችን ሲያሻግር በ40ኛው ደቀቃ የተቆጠረው የምንተስኖት ግብም መነሻው ከግራ መስመር ነበር፡፡

በተቃራኒው የቅዱስ ጊዮርጊስ የቀኝ መስመር በሁለት ምክንያቶች ደካማ ሆኖ ነበር፡፡ የመጀመርያው ከሶስቱ አማካዮች የቀኙን ቦታ የያዘው ምንተስኖት አዳነ የቦታውን ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ከተከላከይ አማካዩ ተስፋዬ ፊት ለፊት በመሆን የቀኝ መስመሩን ክፍት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህም በተለይ ባዬ ገዛኸኝ ጫና እንዲፈጥር እድል ሰጥቶታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ድቻዎች በቦታው (በድቻ ግራ መስመር) ላይ በነበራቸው የቁጥር ብልጫ ምክንያት ፉልባኩ ቢያድግልኝ እና የመስመር አጥቂው ብሪያን እንዲነጣጠሉ አድርጓል፡፡

(ምስል 2/3)

የምንተስኖት አዳነ ሚና

ከላይ እንደተጠቀሰው የምንተስኖት ሚና ነፃ ቢመስልም ግራ አጋቢ ነበር፡፡ ከሶስት አማካዮች የቀኝ መስመሩን ይዞ የገባው ምንተስኖት በቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ወደ ፊት በመጠጋት እንደ ተደራቢ አጥቂ / 10 ቁጥር ሲጫወት ተስተውሏል፡፡ በ40ኛው ደቂቃ ግብ ያስቆጠረበት መንገድም ይህንን ያጠነክርልናል፡፡ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በአግባቡ ባለማራቁ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ የነበረው ምንተስኖት ወደ ግብ ቀይሯታል፡፡

ምንተስኖት በማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ የነበረው ተሳትፎ ጥሩ የነበረ ቢሆንም በመከላከል ላይ የነበረው ታታሪነት እጅግ የወረደ ነበር፡፡ ኳስ በድቻዎች እግር ስትገባ በፍጥነት ትቶት የሄደውን ቦታ የመሸፈን ችግር ሲስተዋልበት የጎንዮሽ እንቅስቃሴ (lateral movement) በማድረግ ለፉልባኩ ቢያድግልኝ ሽፋን መስጠትና ምንያህል በተቀራኒው መስመር ሲያደርገው እንደነበረው ፉልባኩ እና ብሪያን ኡሞኒን የማገናኘት ስራም ሲሰራ አልተስተዋለም፡፡ ድቻዎች በክፍተቱ እምብዛም አልተጠቀሙበትም እንጂ በቀኝ መስመር የነበረው ክፍተት ምንተስኖት በ75ኛው ደቂቃ በፋሲካ አስፋው እስከተቀየረበት ድረስ በጉልህ የሚታይ ነበር፡፡

(ምስል 2/3)

 

ሁለተኛው አጋማሽ

33333

የድቻ 3-2-3-2

2-1 ተመርቶ 2ኛውን አጋማሽ የጀመረው ድቻ አጨዋወቱን ወደ 3-2-3-2 ቀይሯል፡፡ በተለይም ዮሴፍ ዴንጌቶ እና አናጋው ባደግ በ14 እና 15 ቁጥሩ ተቀይረው ሲገቡ ይበልጥ ወደፊት እንዲጠጉ አድርጓቸዋል፡፡

ድቻ በ4 ረድፍ (raws) መጫወቱ በፍጥነት ወደ ግብ እንዲደርስ ቢያግዘውም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን መስበር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ድቻ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በመጓጓት ይመስላል ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ በዘፈቀደ በርካታ ተጨዋቾቻቸውን ወደ ማጥቃት ወረዳ ማስጠጋቱ ቡድኑ ቅርፁን እንዲያጣና እንዲበታተን አድርጎታል፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች የቁጥር ብልጫን መውሰድ ቢችሉም በቁጥር ብልጫው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡

በተለይ ከአጥቂዎቹ ጀርባ የሚገኙት 3 ተጫዋቾች በተደጋጋሚ በመስመሮች መካከል (between the lines) ሰፊ ክፍተት እንዲፈጠር ቢያደርጉም የድቻ የተደራጀ የማጥቃት ቅርፁን ማጣቱ ፈረሰኞቹ ላይ እምብዛም ጫና እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡

(ምስል 3/4)

 

የቀይ ካርድ

በተመሳሳይ ሰአት ከሁለቱም ቡድኖች አንድ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ በመሰናበቱ በሁለቱም በኩል ፈጣን የተጨዋቾች ቅያሪ ተስናግዷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብሪያን ኡሞኒን አስወጥቶ አማካዩ ናትናኤልን ሲያስገባ ድቻ አሸናፊ ሽብሩን አስወጥቶ 3 ቁጥሩን አሰገብቷል፡፡በዚህም ድቻ ፎርሜሽኑን ወደ 3-1-3-2 ሲያሸጋሽግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ወደ 4-4-1 / 4-1-3-1 ለመቀየር ሞክሯል::

(ምስል 4)

4444

ያጋሩ