የጋቦን 2017 ተሳታፊዎች ፕሮፋይል : ሴኔጋል [የቴራንጋ አናብስት]

ሴኔጋል በማጣሪያው ባሳየችው ወጥ ብቃት እና ከሰበሰበቻቸው የተጫዋቾች ጥራት አንፃር ለቻምፒዮንነት ከተገመቱ ሃገራት መካከል ነች፡፡

የቴራንጋ አናብስት ከ2002 የማሊው የአፍሪካ ወዲህ ለፍጻሜ ቀርበው የማያውቁ ሲሆን በማጣሪያዎች የነበራቸውን ድንቅ ግስጋሴም በውድድሮች ላይ ማንፀባረቅ ሳይችሉ በቀላሉ ከምድብ ሲወድቁ ቆይተዋል፡፡ በ2015 የአፍሪካ ዋንጫም ከምድብ ማለፍ ሳይችሉ ተሰናብተዋል፡፡ ሴኔጋል አሁን ላይ የተሻለ ከዋክብቶች በቡድኗ ብትይዝም የውድድር ጫና መቋቋም ላይ ጥያቄ ይነሳባታል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 13

ውጤት፡ ሁለተኛ (2002)

አሰልጣኝ፡ አሊዩ ሲሴ

ሴኔጋል በምድብ ሁለት ከአልጄሪያ፣ ቱኒዚያ እና ዚምባቡዌ ጋር ተደልድላለች፡፡ በምድቡ ውስጥ ከሚገኙት አራት ሃገራት የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት የቻሉት ሰሜን አፍሪካዎቹ አልጄሪያ እና ቱኒዚያ ብቻ ናቸው፡፡

ሴኔጋል በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ጋናን በማሸነፍ የተሳካ አጀማመር ብታሳይም የኃላኃላ ከምድብ ማለፍ ባለመቻሏ ፌድሬሽኑ የአሰልጣኝ ለውጥ እንዲያደርግ አስገድዶታል፡፡ አሊዩ ሲሴ በ2002 ታሪካዊው የብሩኖ ሜትሱ ቡድን ውስጥ የነበረ ሲሆን ቡድኑን ከተረከበ ወዲህ ከፍተኛ መሻሻልን አሰይቷል፡፡ ሲሴ 4-3-3 የተጫዋቾች አደራደር ስርዓትን መከተል በአብዛኛው ቢመርጥም እንደተጋጣሚ ቡድኑ የጨዋታ ስርዓቱን መለወጥ መቻሉ ሴኔጋልን በከፍተኛ ሁኔታ ጠቅሟታል፡፡ ከዚህ ቀደም ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ያሰለጠናቸው አብዛኞቹ ተጫዋቾች አሁንም በዋናው ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አሉ፡፡

ሲሴ ከሴኔጋል ጋር የአፍሪካ ዋንጫን የሚያሸነፍ ከሆነ ድሬድ ፀጉሩን እንደሚቆረጥ ቃል ገብቷል፡፡ በውድድሮች ላይ ያለውን ጫና መቋቋም የሚችል ቡድን ወደ ጋቦን ይዞ ከሄደ ምንአልባትም ሴኔጋል የተሸለ ውጤት ለማምጣት ትችላለች፡፡

ተስፋ

ወጥነት ያለው ብቃት የሚያሳዩ ተጫዋቾችን መያዙ ለሴኔጋል አንድ ተስፋ ነው፡፡ እንዲሁም በቴክኒክ ብቃታቸው ላቅ ያሉ ተጫዋቾችን ብድኑ ይዟል፡፡ ሳድዮ ማኔን የመሰለ ድንቅ ተጫዋች በቡድኑ የተካተተ ሲሆን ማኔ በማጥቃቱ በኩል ያለው ተሳትፎ መልካም የሚባል ነው፡፡

የተከላካይ መስመሩም ሆነ የአማካይ መስመሩ ጠንካራ እና ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች መዋቀሩ ሌላው የቡድኑ መልካም ጎን ነው፡፡ በማጣሪያው ደከም ያሉ ቡድኖች ቢገጥምም ቡድኑ ከትልቅ ደረጃ ለመወዳደር እንግዳ አለመሆኑ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይረዳዋል፡፡

ስጋት

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ከትልልቅ ቡድኖች ጋር በሚደረጉ ጨዋታዎች ቡድኑ ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ ይህም የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞቸው ላይ እክል እንዳይፈጥር ያሰጋል፡፡ የተከላካይ መስመሩ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች ቢዋቀርም በተደጋጋሚ የሚታዩ የአቋም መዋዠቆች ለሲሴ የራስ ምታት ሆኗል፡፡ በግብ ጠባቂ በኩልም ብሄራዊ ቡድኑ የሚተማመንበት ግብ ጠባቂ የለም፡፡ ይህም ከተከላካይ መስመሩ መሳሳት ጋር ተደማምሮ ነገሮችን ያከብዳሉ፡፡ እንደአልጄሪያ ካሉ በአጥቂ መስመራቸው ላይ ጠንካራ የሆኑ ሃገራትን ስትገጥምም ይህ የተከላካይ ስፋራ ዋጋ እንዳያስከፍላት ይሰጋል፡፡ እንዲሁም ጫናን መቋቋም ላይ ቡድኑ ካልሰራ አሁንም ልክ እንደ2012 የአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ እንዳይሰናበት ይሰጋል፡፡

የሚጠበቁ ተጫዋቾች

የቴራንጋ አንበሶቹ ኮከብ ተጫዋች ሳድዮ ማኔ ነው፡፡ ማኔ በማጣሪያ ጉዞው ላይ ግቦች ከማስቆጠር ባለፈ በተደጋጋሚ የተጋጣሚን የተከላካይ ክፍል እረፍት በማሳጣት ይታወቃል፡፡ ሴኔጋል ከማኔ ብዙ ብትጠብቅም የሚገርም አይሆንም፡፡

ሴኔጋል እንደ ማሜ ቤራም ዲዩፍ እና ሙሳ ሶ አይነት አጥቂዎችንም ይዛለች፡፡ በስፔን ተወልዶ ለሴኔጋል መጫወትን የመረጠው የላዚዮው ኮከብ ኬታ ባልዴ ዴያዎም ሌላው መታየት ያለበት ተጫዋች ነው፡፡ የ21 ዓመቱ ኬታ ለሴኔጋል በተሰለፈባቸው እያንዳንዱ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ለሚቆጠር አንድ ግብ ተሳታፊ ነው፡፡ በወረቀት ላይ ሲታይ አስፈሪ የአጥቂ መስመር ያለው ቡድን ነው ሴኔጋል፡፡ በጣሊያን የሚጫወተው ተከላካዩ ካሊዱ ኩሊባሊ ሌላው ሊታይ የሚገባ ተጫዋች ነው፡፡

የማጣሪያ ጉዞ

ሴኔጋል በምድብ 11 ከብሩንዲ፣ ናሚቢያ እና ኒጀር ጋር ተደልድላ ነበር፡፡ ስደስቱንም የማጣሪያ ጨዋታ ያሸነፈች ብቸኛዋ ቡድን ስትሆን ማግኘት ከነበረባት 18 ነጥብ ሁሉንም በማሳካት ነው በተደላደለ ሁኔታ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፍ የቻለችው፡፡ 13 ግቦችን ተጋጣሚዎቿ መረብ ላይ ስታሳርፍ በአንፃሩ ሁለት ግቦችን አስተናግዳለች፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂ

አቡዱላሂ ዲያሎ (ካይኩር ሪዚስፖር/ቱርክ)፣ ሰይዶ ንዳዬ (ኤንጂቢ ኒያሪ ታሊ/ሴኔጋል)፣ ካዲም ንዳዬ (ሆሮያ/ጊኒ)

ተከላካዮች

ሞቦጂ ካራ (አንደርሌክት/ቤልጂየም)፣ ካሊዱ ኩሊባሊ (ናፖሊ/ጣሊያን)፣ ሼክ ቦያ ምቤንጉ (ሴንት ኢቲየን/ፈረንሳይ)፣ ዛርጎ ቱሬ (ሎሪዬ/ፈረንሳይ)፣ ሳሊዮ ሲስ (ቫለንሲየንስ/ፈረንሳይ)፣ ላሚን ጋሳማ (አላንያስፖር/ቱርክ)

አማካዮች

ኢድሪሳ ጋና (ኤቨርትን/እንግሊዝ)፣ ቼኮዎ ኮያቴ (ዌስትሃም ዩናይትድ/እንግሊዝ)፣ ቼክ ንዶዬ (አንገርስ/ፈረንሳይ)፣ መሃመድ ድያሜ (ኒውካስል ዩናይትድ/እንግሊዝ)፣ ፓፓ ዲዮፕ (ኤስፓኞል ባርሰሎና/ስፔን)፣ ፓፓ ንዳዬ (ኦስማንሊስፖር/ቱርክ)፣ ሄነሪ ሳቪት (ሴንት ኢቲየን/ፈረንሳይ)

አጥቂዎች

ኬታ ባልዴ (ላዚዬ/ጣሊያን)፣ ሙሳ ሶ (ፌነርባቼ/ቱርክ)፣ ሰይዶ ማኔ (ሊቨርፑል/እንግሊዝ)፣ ፋማራ ዴዴሁ (አንገርስ/ፈረንሳይ)፣ ማሜ ቤራም ዲዩፍ (ስቶክ ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ሙሳ ኮናቴ (ሲዮን/ስዊዘርላንድ) 

ሴኔጋል በምድብ ሁለት ቱኒዚያን ዕሁድ ትገጥማለች፡፡

Leave a Reply