የጨዋታ ሪፓርት | ሲዳማ ቡና የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ የሜዳው ውጪ ድል አስመዝግቧል 

በ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወደ አዲስ አበባ ያቀናው ሲዳማ ቡና ከተከከታይ ነጥብ መጣሎች በኃላ አዲስ አበባ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ዳግም ወደ አሸነፊነት ተመልሷል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በመሀል ሜዳ ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴን ያደረጉ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ወደፊት ቶሎ ቶሎ በመድረስ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ በአንጻሩ ባለሜዳዎቹ አዲስ አበባ ከተማዎች በመሀል ሜዳ ኳሶችን ከመቀባበል በዘለለ ወደ ፊት በመሄድ የግብ ሙከራ በመፍጠር በኩል ችግር ታይቶባቸዋል፡፡

በ5ኛው ደቂቃ ፍፁም ተፈሪ ከረጅም ርቀት ሞክሮ ተክለማርያም ሻንቆ ያዳነበት እንዲሁም በ9ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ፍሰሀ ያሾለከለትን ናይጄሪያዊዉ አጥቂ ላኪ ሳኒ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ በሲዳማ ቡና በኩል ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ በተመሳሳይ በ25ኛው ደቂቃ ፍፁም ተፈሪ ከርቀት የመታውን የቅጣት ምት ተክለማርያም ያዳነበት በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ግብ ካደረጓቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበረች፡፡

በ41ኛው ደቂቃ ከአዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል በቅርብ ርቀት የተገኘውን ቅጣተት ምት አዲስ ግደይ መትቶ አዲስ አበባ ተከላካዮች ሲመለስ በቅርብ ርቀት ይገኝ የነበረው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ግሩም አሰፋ በቀጥታ በመምታት የቡድኑን ወሳኝ የማሸነፍያ ግብ አስቆጥሯል፡፡

በጨዋታው የሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባ ከመጀመሪያው በተሻለ ቀጥተኝነትን ጨምረው በመምጣት እጅግ በርካታ ኳሶችን ከመስመር ላይ በማሻማት የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ ነገርግን ይህ ጥረታቸው በቀላሉ በሲዳማ ቡና ተከላካዮች በተለይም በአበበ ጥላሁን እና ሳንዲይ ሙቱኩ በቀላሉ እየተገጩ ሲመለሱ ተስተውሏል፡፡ በአንጻሩ ሲዳማ ቡናዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ወደ ኃላ አፈግፍገው ተጫውተዋል፡፡

ሌላኛው በዚህ አጋማሽ ከታዩ ክስተቶች መካከል የሲዳማ ቡና ቡድን የተጫዋቾች ለውጥ በሚያደርግ ጊዜ ተቀይረው የሚወጡት ተጫዋቾች በእነሱ ምትክ ለሚገባው ተጫዋች መጋጫቸውን እየሰጡ የሚወጡበት አጋጣሚ በተመልካቾች ዘንድ አግራሞትን የጫሩ ክስተቶች ነበሩ፡፡ በዚህም ተቀይረው የሚገቡት ተጫዋቾች መጋጫውን አድርገው እስኪገቡ ድረስ ቡድኑ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች ሲጫወት ተስተውሏል፡፡

ድሉን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ከተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣል በኃላ ከሜዳው ውጪ የነበረውን አስከፊ ሪከርድ በማሻሻል ጭምር ነጥቡን ወደ 18 አሳድጎ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዲስ አበባ ከተማዎች ተከታታይ ስምንተኛ ጨዋታ በመሸነፍ አሁንም በሊጉ ግርጌ ተቀምጠዋል፡፡

ያጋሩ

Leave a Reply