ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 አዳማ ከተማ | የአሰልጣኞች አስተያየት 

ጸጋዬ ኪዳነማርያም – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለ ጨዋታው

“ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ከሜዳ ውጪ ተሸንፈን ነበር የውድድር ዘመኑን የጀመርነው፡፡  ከዛ በኃላ በነበሩን ጨዋታዎች ቡድናችንን አሻሽለን ለመቅረብ ሞክረን ሁለት ጨዋታዎችን በተከታታይ አሸነፈን ነበር፡፡ ከዛ በኃላ ቋሚ ተጫዋቾቻችን በጉዳት እና በግል ችግር የተነሳ ከድሬዳዋው ጨዋታ ጀምሮ እስካሁን አልገቡም ነበር፡፡ ነገርግን በዛሬው ጨዋታ ሁለቱን ግብ አስቆጣሪዎች ጨምሮ ጋብሪኤል አህመድ የመሳሰሉ ተጫዋቾች ተመልሰዋል፡፡ የእነዚህ መመለስ ለቡድኑ ጠቀሜታ እና ሀይል ሰጥቷቸዋል፡፡ ትልቁ ነገር በዛሬው ጨዋታ ቡድናችን ከአንተነህ በስተቀር የተሟላ ቡድን ይዘን ቀርበናል ፤  ስለዚህ የእነዚህ ልጆች መመለስ ለቡድናችን ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡”

በቀጣይ በሊጉ ስላላቸው እቅድ

“የቡድን ግንባታ በሁለት የተከፈለ ነው፡፡ አሁን እንዳያችሁት ከአንተነህ ውጪ ከምንጠቀማቸው ቋሚ 11 ተጫዋቾች ውስጥ 10 ተጫዋቾች ዛሬ ሜዳ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሌላኛው ሁለተኛው ተጠባባቂ ሀይላችን ደግሞ በወጣት ተጫዋቾች የተሞላ ነው ፤ የመጀመሪያው ሀይል ተሟልቶ ወደ ሜዳ ስንገባ ልምድ ያላቸው ስለሚሆኑ ውጤታችን ጥሩ ነው የሚሆነው ፤ ነገርግን ወደ ክልል ስንወጣ ቋሚ ተጫዋቾች በሚጎዱብን ጊዜ በልምድ ማጣት በሚሰሩ ስህተቶች ነጥብ እያጣን እንገኛለን፡፡ ነገርግን እነዚህ ወጣቶች ለተወሰነ ደቂቃም ቢሆን ቀይሬ እያስገባሁ ልምድ እንዲያገኙ በማድረግ በሁለተኛው ዙር ተጨማሪ አንድ ወሳኝ አጥቂ በማስፈረም በሊጉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንጥራለን፡፡”

አሸናፊ በቀለ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ጥሩ የመሸናነፍ ትግል የተደረገበት ጨዋታ ነበር፡፡ ስለዚህ ውጤቱን በፀጋ ተቀብለናል፡፡”

“ለማሸነፍ ነበር የመጣነው ፤ ያገኘናቸውን ወርቃማ እድሎች አልተጠቅምንም እነዛን እድሎች ተጠቅመን ቢሆን ኖሮ ነገሮች እንደዚህ አይሆኑም ነበር ፤ የልጆቼ መጓጓት እና ስሜታዊ መሆን እንደምንፈልገው እንዳናደርግ አድርጎናል፡፡ ነገርግን አሁንም ከመሪዎቹ ተርታ ስለምንገኝ ገና ቀሪ በርካታ ጨዋታዎች አሉን፡፡ ስለዚህ ገና ማን ቻምፒዮን እንደሚሆን አናውቅም፡፡”

በሊጉ መሪነት ስለመዝለቅ

“ውድድሮች ገና ናቸው ፤ እኛ የምናስበው በሊጉ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነን መቅረብ እና ለተመልካቹ ጥሩ ጨዋታን ማሳየት ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው ስለዚህ ውጤታማ ሆነን ለመቀጠል እንጥራለን፡፡ እንደሚታወቀው በተከታታይ ሁለት አመታት ሜዳሊያ ውስጥ ገብቶ ያጠናቀቀ ቡድን ነው ፤ ስለዚህ ጥንካሬያችንን ይዘን እንድንቀጥል የኔ እና የልጆቼ ፍላጎት ነው፡፡”

የተጫዋቾች ስነምግባር

“ለማሸነፍ ሁሌም ቁርጠኛ ሆነን ነው ሜዳ የምንገባው፡፡ አንዳንዴ ነገሮች እንደታሰበው ሳይሆን ሲቀር ልጆቼ ስሜታዊ ሆነዋል፡፡ ምክንያቱም ይህንን ስሜታዊነት የፈጠረው ረዳት ዳኛው እና የመሀል ዳኛው አለመናበብ ነው ፤ ነገር ግን ተመልካችን ሊያስቀይም የሚችል ተግባር ስለሆነ በቀጣይ አሻሽለን እንቀርባለን፡፡”

ስለዳኝነት

“ዳኛ ሁሌም ትክክል ነው ፤ ተጫዋቾች በርካታ የግብ እድሎችን አምክነዋል፡፡ ስለዚህም ምንም ልላቸው አልችልም ፤ ልክ እንደዛው ዳኛው የመሠለውን ውሳኔ ወስኗል፡፡”

ያጋሩ

Leave a Reply