ጋቦን 2017 | የምድብ አንድ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል

የ2017 ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ ቅዳሜ ሊበርቪል ላይ ሲጀመር በስታደ አሚቴ የምድብ አንድ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ አዘጋጇ ጋቦን በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ እየተሳተፈች ከምትገኘው ጊኒ ቢሳው ጋር 1-1 ስለትለያይ ካሜሮን እና ቡርኪናፋሶ በተመሳሳይ የአቻ ውጤት ጨዋታቸው ጨርሰዋል፡፡

የመክፈቻው ስነ-ስርዓት ላይ እንደተጠበቀው ብዙ ደጋፊ ያልተገኘ ሲሆን የፕሬዝደንት አሊ ቦንጎ መንግስት የመግቢያ ትኬቶችን በነፃ ሲያድል እንደነበረ ተነግሯል፡፡ ቀስ በቀስ ስታዲየሙ ቢሞላም እንደተጠበቀው የደጋፊ ብዛት አልነበረም፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ጋቦን የእንቅስቃሴ ብልጫን አብዝቶ መከላከልን በመረጡት ጊኒ ቢሳዎች ላይ ወስዳ ነበር፡፡ የማሪዮ ለሚና በመጀመሪያው 45 ጥሩ አለመሆን እንዲሁም የማሊክ ኢቮና እና ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ ጥምረት አለመዳበር ጥቋቁር ግስላዎቹን ግብ እንዳያስቆጥሩ አግዷቸዋል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ በኢቮና እና በ45ኛው ደቂቃ በሊማና ያደረጓቸው ሙከራዎች የሚጠቀሱ አስደንጋጭ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ጋቦኖች ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን በ2012 እና 2015 የጋቦንን የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ግቦች ያስቆጠረው ኦባሚያንግ በጨዋታው ጥሩ ከተንቀሳቀሰው ቦአንጋ የተሻገረለትን ጥሩ ኳስ ተጠቅሞ ሃገሩን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ ጊኒ ቢሳዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡ በተለይ ከቆሙ ኳሶች የጋቦንን የተከላካይ ስፍራ ሲፈትኑ የነበሩት ተኩላዎቹ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ጀአራይ ሱዋሬስ በግንባሩ በመግጨት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል፡፡

የጊኒ ቢሳው አማካይ ሆዜ ሉዊስ ሜንዴዝ ሎፔዝ (ዚዚንሆ) የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጧል፡፡ ጊኒ ቢሳውም በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ ባደረገችው ጨዋታ ነጥብ ማግኘት ችላለች፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በስታዲየም የተገኘው ደጋፊ የጋቦን ብሄራዊ ቡድን ላይ ተቋውሞን አሰምቷል፡፡

 

ምሽት 4 ሰዓት ላይ በተደረገው ሁለተኛው የምድብ አንድ ጨዋታ ካሜሮን ከቡርኪናፋሶ ጋር ነጥብ ተጋርታለች፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴ እና የተመልካችን ቀልብ በሳበው በዚህ ጨዋታ የማይበገሩት አናብስቶች በመጀመሪያው አጋማሽ በቤንጃሚን ሙካንጆ የቅጣት ምት ግሩም ግብ መሪ መሆን ችሏል፡፡ ፈረሰኞቹ በሁለተኛው አጋማሽ የሱፉ ዳዮ ከቅርብ ርቀት በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተጫዋች አሊያን ትራኦሬ ከቡርኪናፋሶ ሆኗል፡፡

የምድቡ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በመጠናቀቃቸው ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ይበልጥ ፈታኝ እና ወሳኝ ያደርጋቸዋል፡፡

ዛሬ በምድብ ሁለት ምሽት 1፡00 ላይ አልጄሪያ ዚምባቡዌን ስትገጥም ምሽት 4፡00 ላይ ሴኔጋል ከቱኒዚያ ይጫወታሉ፡፡

 

የፎቶ ምንጮች፡ ጋርዲያን እና ካፍ

Leave a Reply