አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ በፌዴሬሽኑ ተመረጡ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቀጣዩን የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መርጦ መጨረሱንና ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶን ለመቅጠር መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ከ20 ቀናት በፊት ለብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ያመለከቱ 27 አሰልጣኞችን ዝርዝር ይፋ አድርጎ የነበረው ፌዴሬሽኑ በሂደት የእጩዎችን ሲቪ ተመልክቶ 4 አሰልጣኞችን ለመጨረሻ እጩነት አቅርበዋል፡፡ አሁን ፌዴሬሽኑ የፖርቱጋላዊው አሰልጣኝን ሲቪ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች የተሻለ ነው ብሎ በማመኑ የቀድሞውን የጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመቅጠር ወስኗል፡፡ በቀጣዮቹ 2 ቀናትም አሰልጣኙ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ድርድር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ጃንዋሪ 18 ቀን 1957 በህንዷ ጎአ የተወለዱት የ57 አመቱ ማርያኖ በአሰልጣኝነት አለምን ዞረዋል፡፡ ከ2003 ጀምሮ የጋና ብሄራዊ ቡድንን ፣ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትሱ አል ናስር ፣ የአንጎላው ሪክሬቲቮ ዶ ሊቦሎ ፣ የሳኡዲ አረቢያውን አል-ቃዲሲያህ ፣ የፖረቱጋሎቹን ናቫል ዲ ማዮ እና ማሪቲሞ በዋና አሰልጣኝነት ሲያሰለጥኑ በሩሲያዎቹ ዳይናሞ ሞስኮ እና ኩባን ክራንስዶር ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል፡፡

አሰልጣኙ በስራ ማመልከቻቸው ላይ የቦሩሲያ ዶርትሙንድ ምክትል አሰልጣኝ ሆነው መስራታቸውን ገልፀው የጋና ብሄራዊ ቡድንን መረከባቸውና ኋላ ላይ አሰልጣኙ በክለቡ በምክትል አሰልጣኝነት አለመስራታቸው ተረጋግጦ የመነጋገርያ ርእስ ለመሆን በቅተው ነበር፡፡

አሰልጣኝ ለመቅጠር ከምልመላ ይልቅ በሲቪ ማወዳደርን የመረጠው የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቀውን ስራ በውጤታማነታቸው የማይታወቁ እንዲሁም ያልሰሩበትን ክለብ በሲቪያቸው ለሚያካትቱ አሰልጣኝ መስጠቱ በአመራሮቹ ላይ ያለውን ጥርጣሬ የሚያጎላ ሆኗል፡፡

በተያያዘ ፌዴሬሽኑ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝን በዚህ ሳምንት እንደሚያሳውቅ አስታውቋል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ