የጨዋታ ሪፓርት| ኤሌክትሪክ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል አስመዝግቧል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻም ከድል ጋር ተገናኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻን ያስተናገዱት ቀዮቹ 2-1 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችሏል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከወላይታ ድቻዎች በተሻለ በተደጋጋሚ ጫና በመፍጠር ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በተለይም በ7ኛው ደቂቃ ፍፁም ገብረማርያም ከመሀል ያሻገረለትን ኳስ ኢብራሂም ፉፋኖ የግሉን ጥረት ተጠቅሞ ወደ ድቻ የግብ ክልል ከገባ በኃላ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ለኤሌክትሪክ የመጀመርያ ግብ ልትሆን የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡

ከ15 ደቂቃ በኃላ ወደ ጨዋታው የተመለሱ የሚመስሉት ወላይታ ድቻዎች በጥልቀት በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ ነገርግን በዚሁ የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ እና የግብ ሙከራ በማድረግ የተሻሉ ነበሩ፡፡

በ36ኛው ደቂቃ አሸናፊ ሽብሩ ከቆመ ኳስ ያሻማውን የድቻ ተከላካዮች ሲመልሱ የግብ ክልሉ ጠርዝ አካባቢ የነበረው አዲስ ነጋሽ በቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክርሞ ኳሷ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ እንዲሁም በድጋሚ በ39ኛው ደቂቃ ላይ አወት ገ/ሚካኤል ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አማኑኤል ተሾመ ወደ ውጪ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ለጥቂት በራሱ ግብ ላይ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቀሩት ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች መሀል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

 

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ የመሸናነፍ ፉክክር እና እልህ የታየበት ሆኖ አልፏል፡፡

በዚህም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ በ48ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ተሻገር ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት በአንበላቸው አዲስ ነጋሽ አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታውን 1-0 መምራት ችለዋል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ኤሌክትሪኮች ከተከላካዮች በረጃጅሙ በሚላኩ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ኳሶቹ ግን እምብዛም የተሳኩ አልነበሩም፡፡

በ57ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ተሾመ በግምት ከ28 ሜትር አካባቢ አክርሮ በመምታት የሞከረውን ኳስ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አቡ ሱሌይማን ባስደናቂ ሆኔታ አድኖበታል፡፡ በአማኑኤል ተሾመ ሙከራ የተነቃቁት ወላይታ ድቻዎች በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ድጋፍ ታግዘው ወደ ጨዋታው ለመመለስ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል፡፡ በዚህም በሁለቱም መስመሮች በሚገኙ ተጫዋቾቻቸው ኳስ ቶሎ ቶሎ ወደፊት ለማድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡

ነገርግን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ75ኛው ደቂቃ  በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ኢብራሂም ፉፋኖ ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም በግሩም ሆኔታ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ለባዶ ማሳደግ ችሏል፡፡

ግቧን ተከትሎ ከግቧ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከድል ጋር ተራርቀው የቆዩት የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሰአት በማባከን እና በጥብቅ የመከላከል ስራ ላይ ተጠምደው አሳልፈዋል፡፡

በ81ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው መሳይ አጪሶ በቀጥታ መቶ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሎ ነበር፡፡ ነገር ግን በቀሩት ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም ኤሌክትሪኮች በአግባቡ ተከላክለው ውጤቱን አስጠብቀው ወጥተዋል፡፡

ድሉ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ድል ሲሆን ነጥባቸውን ወደ 10 ከፍ በማድረግም ደረጃቸውን ወደ 12ኛ ከፍ ማድረግ ችለዋል፡፡

Leave a Reply