ጋቦን 2017 | ሴኔጋል ስታሸንፍ አልጄሪያ ነጥብ ተጋርታለች

የቶታል 2017 አፍሪካ ዋንጫ እሁድ በምድብ ሁለት በተደረጉ ጨዋታዎች ቀጥለው ተደርገዋል፡፡ ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ዚምባቡዌ ከአልጄሪያ ጋር አቻ ስትለያይ ሴኔጋል ቱኒዚያን 2-0 አሸንፋለች፡፡ ጨዋታዎቹ ፍራንስቪል ላይ ነበር የተደረጉት፡፡

አልጄሪያ እንደምታሸንፍ ተጠብቆ በነበረው ጨዋታ ዚምባቡዌ ከበረሃ ቀበሮዎቹ ጋር 2-2 አቻ ወጥተዋል፡፡ ጦረኞቹ መልካም የሆነ አጀማመር የነበራቸው ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ የፈጠሯቸው የግብ ማግባት ሙከራዎች የአልጄሪያን የተከላካይ ክፍል ድክመት በግልፅ አሳይተዋል፡፡ ካማ ቢሊያት በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች የሞከረው ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል፡፡ ሪያድ ማህሬዝ አልጄሪያን በ12ኛ ደቂቃ መሪ ሲያደርግ ኩዳኩዋሼ ማሃቺ ከአምስት ደቂቃዎች በኃላ ዚምባቡዌን አቻ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያው ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ በ29ኛው ደቂቃ ለጦረኞቹ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጡ ሲሆን ፍፁም ቅጣት ምቱን ናያሻ ሙሺክዊ አስቆጥሮ ሃገሩን ያልተጠበቀ መሪ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አልጄሪያዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ተጭነው ሲጫዋቱ ዚምባቡዌ አልፎ አልፎ በሚደረጉ አደገኛ መልሶ ማጥቃቶች ለመጫወት ሞክራለች፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ አልጄሪያው ሪየስ ሙቡህሊ እንደመጀመሪያ አጋማሽ ሁሉ ያለቀላቸውን ኳሶች በማዳን ድንቅ ሁኖ አምሽቷል፡፡ ማህሬዝ የአልጄሪን የአቻነት ግብ በ82ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፋል፡፡ ሃገራቱ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡ በጨዋታው ሁለት ግብ ያስቆጠረው ማህሬዝ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል፡፡

በምድቡ ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ሴኔጋል ቱኒዚያን 2-0 በማሸነፍ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያሳካች የመጀመሪዋ ሃገር ሁናለች፡፡ ሳይዶ ማኔ በ10ኛው ደቂቃ የቴራንጋ አናብስቶቹን በፍፁም ቅጣት ምት መሪ ሲያደርግ ሞዶ ካራ በድንቅ ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ልዩነቱን ወደ 2 አስፍቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋመሽ ብዙም ወደፊት በመሄድ ጥሩ ያልነበሩት የካርቴጅ ንስሮቹ በአህመድ አኪያቺ፣ የሱፍ ሳክኒ እና ዋሂብ ካዝሪ አማካኝነት በሁለተኛው 45 ግብ ለማስቆጠር ያልተሳካ ሙከራ አድርገዋል፡፡ በሁለተኛው 45 ሴኔጋል በጠንካራ መከላከል ወደ ሜዳ መግቧቷ ቱኒዚያን ውጤቱን ከመቀልበስ እግዷታል፡፡ የሴኔጋሉ ግብ ጠባቂ አብላሂ ዳያሎ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ሴኔጋል ምድቡን በሶስት ነጥብ መምራት ጀምራለች፡፡

የምድብ ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲደረጉ የካቻምና አሸናፊዋ ኮትዲቯር ቶጎን ምሽት 1፡00 ላይ ስታስተናግድ ዲ.ሪ. ኮንጎ ከሞሮኮ ምሽት 4፡00 ላይ በስታደ ኦየም ይጫወታሉ፡፡

የፎቶ ምንጭ ካፍ

Leave a Reply