የጋቦን 2017 ተሳታፊዎች ፕሮፋይል | ቶጎ [ወፎቹ]

ቶጎ በኢማኑኤል አዴባዮር እና ክላውድ ለርዋ መሪነት ከ2013 በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ተመልሳለች፡፡ በ2013 ለሩብ ፍፃሜ የበቃችው ቶጎ በ2017 በጥሩ ሁለተኝነት የማጣሪያ ምድቧን አጠናቅቃ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ተመልሳለች፡፡

በአህጉሪቱ ውድድር እዚህ ግባ የሚባል ውጤት የሌላት ቶጎ ዘጠነኛ የአፍሪካ ዋንጫቸው የሆኑትን ፈረንሳዊው ታዋቂ አሰልጣኝ ለርዋን ይዛለች፡፡ (ለርዋ ከቶጎ በበለጠ በርካታ የአፍሪካ ዋንጫዎችን ተካፍለዋል)፡፡ ከለርዋ መምጣት በኃላ ለውጥ ያሳየችው ቶጎ አስቸጋሪ ምድብ ሩብ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ፈታኝ ሁኔታ ይጠብቃታል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 7

ውጤት፡ ሩብ ፍፃሜ (2013)

አሰልጣኝ፡ ክላውድ ለርዋ

ቶጎ በምድብ ሶስት ከ2015 ቻምፒዮኗ ኮትዲቯር፣ ሞሮኮ እና ዲ.ሪ. ኮንጎ ጋር ተመድባለች፡፡ ቤልጂየማዊው አሰልጣኝ ቶም ሴንትፊትን ከተሰናበቱ በኃላ ወደ ቶጎ የመጡት ክላውድ ለርዋ በ1988 ከካሜሮን ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮን የሆኑ ሲሆን በ2015 ኮንጎ ብራዛቪልን ለሩብ ፍጻሜ አብቅተዋል፡፡ ጠንቋዩ በሚል ቅፅል ስም የሚጠሩት አንጋፋው አሰልጣኝ ለርዋ በበርካታ የመካከለኛው እና ምእራብ አፍሪካ ሃገራት የሰሩ መሆኑና ሰፊ የሆነ እና የካበተ የአፍሪካ ዋንጫ ልምድ ያላቸው መሆኑ ለቡድኑ መልካም ነው፡፡ በ2013 ሩብ ፍፃሜ ከደረሰው ቡድን ውስጥ 11 አሁንም ሲገኙ ልምድ ያላቸው እና ጥሩ መስራት የሚችሉ ተጫዋቾች በቡድኑ አሉ፡፡ የቡድን ጥልቀት ግን በቶጎ ላይ አይታይም በተለይ በተቀያሪ ወንበር ላይ ብቁ የሆኑ ተጫዋቾች ቡድኑ የሉትም፡፡

ቶጓዊው የእግርኳስ ጋዜጠኛ ስቲቨን ላቮን ስለሃገሩ ብሄራዊ ቡድን ተስፋ ፣ ስጋት እና ሌሎችም ጉዳዮች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ስቲቨን የafricatopsports.com ፀሃፊ ነው፡፡

ስለምድብ ሶስት

በእኔ አስተያየት ምድብ ሶስት አፍሪካ ዋንጫው ላይ ካሉ ፈታኝ ምድቦች መካከል ነው፡፡ ሶስት የቀድሞ ቻምፒዮኖች እና የተሻለ ውጤቷ ሩብ ፍፃሜ የሆነው ቶጎ ትገኛለች፡፡ ቶጎ በውድድሩ ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ነው ወደ ጋቦን የመጣችው፡፡ ኮትዲቯር ያለምንም ጥርጥር ምርጥ ቡድን እና ምርጥ ተጫዋቾችን የያዘች ናት፡፡ በተለይ ፍራንክ ኬሲ እና ጆናታን ኮዲጃ ያንፃባርቃሉ የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ሞሮኮም ጥሩ ቡድን አላጥ ግን የቤልሃንዳ፣ ታናን፣ ቡፋል እና አማርባት አለመኖር ነገሮችን አስቸጋሪ ያደርጉባታል፡፡ ዲ.ሪ ኮንጎ በምድብ ውስጥ ማግኘት የማትፈልገው ቡድን ነው፡፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ በሃገሯ ተወላጅ አሰልጣኝ እየተመራች ቀጣይነት የነበረው እድገትን አሳይታለች፡፡

 ተስፋ

“የቶጎ አላማ ልክእንድ 2013 የተሻለ ደረጃ መድረስ ነው፡፡ ሰዎች ይህ ነገር ቀላል እንዳልሆነ ያውቃሉ፡፡ ቡድኑ የያዛቸው ተጫዋቾች በአብዛኛው በሊጎቻቸው እምብዛም የመጫወት እድል ያላገኙ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የአካል ብቃታቸው ላይ ገና ይቀራቸዋል፡፡ ቢሆንም የማሸነፍ ፍላጎት እና ቆራጥነት ስላላቸው የተሻለ ነገር ማሳየት ይችላሉ፡፡ ከዚህም በላይ የአፍሪካ ዋንጫን ከማንም በላይ ጠንቅቀው የሚያውቁ አሰልጣኝ አለን፡፡ ክላውድ ለርዋ ይህ 9ኛ የአፍሪካ ዋንጫቸው ነው ስለዚህም ልምዳቸው ቶጎን በጣም ይጠቅማል፡፡”

ስጋት

“ሩብ ፍፃሜ መድረስ ከቻልን በጣም ጥሩ ውጤት ነው፡፡ የእግርኳስ ፌድሬሽኑ እየገነባ ያለው ቡድን ለ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ስለሆነ ይህ ቡድን ጉዞው እስከየት ነው የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ነገሮች ቀስ በቀስ ጨዋታ ከጨዋታ ነው የምናየው ቢሆንም ይህ ስጋት አለኝ፡፡”

የሚጠበቁ ተጫዋቾች

“ከአዲባዮር ውጪ ሰዎች ፎዶ ላብን እንዲመለከቱ እመክራለው፡፡ ወጣቱ ላብ በሞሮኮው ሬኔሳንስ በርኬን ነው የሚጫወተው፡፡ ፍይድ አይቲ፣ ቤቦ፣ አታኮራ በብሄራዊ ቡድን ውስጥ ወሳኝ በመሆናቸው ሰዎች ቢመለከቷቸው ጥሩ ነው እላለው፡፡”

ቶጎ በአጣብቂኝ ውስጥ ሆኗ አፍሪካ ዋንጫው የተቀላቀለች ሲሆን ከፊቷ ሶስት ጥሩ የአፍሪካ እግርኳስ ሃገራት ተደቅነዋል፡፡ የለርዋ መኖር በጎ ቢሆንም የቡድኑ ጥልቀት እስከዚም መሆን ቶጎን ከምድብ እንዳትሰናበት ያስብላል፡፡ በተወሰኑ ከዋክብ ትከሻ ላይ የወደቀው ቡድን ላይ የ2013ቱ ስኬትን በደንብ የሚረዱ ተጫዋቾች መኖራቸው ለቶጎ መልካም ይመስላል፡፡

የማጣሪያ ጉዞ

ቶጎ በምድብ አንድ ከቱኒዚያ፣ ላይቤሪያ እና ጅቡቲ ጋር ነበር የተደለደለችው፡፡ ቶጎ በጥሩ ሁለተኛነት አፍሪካ ዋንጫው ስትቀላቀል ኢትዮጵያን እና ቤኒንን በልጣ ነው፡፡ በ11 ነጥብ ከምድቧ ሁለተኛ ሆኗ የጨረሰች ሲሆን ሶስት አሸንፋ አንድ አቻ ወጥታ በቱኒዚያ ደግሞ ከሜዳዋ ውጪ ተሸንፋለች፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ሴድሪክ ሜንሳህ (ለ ሞን/ፈረንሳይ)፣ ኮሲ አጋሳ (ሳንስ ክለብ/ቶጎ)፣ ባባ ቻጎኒ (ማርሜንድ/ፈረንሳይ)

ተከላካዮች

ሃኪም ኦሮ ሳማ (ኤኤስ ቶጎ ፖርት/ቶጎ)፣ ሰርጅ አካክፖ (ትራብዞንስፖር/ቱርክ)፣ አብዱልጋፋር ማማህ (ዳሲያ/ሞልዶቫ)፣ ቪንሰንት ቦሱ (ያንግ አፍሪካንስ/ታንዛኒያ)፣ ሳድኤት ኦሮ አኮሪኮ (አል ካሊጅ ሳሃት/ሳውዲ አረቢያ)፣ ዳኮናም ጄን (ሴንት ትሮንድ/ቶጎ)

አማካዮች 

ኮፊ አትቾ (ዶይቶ ደ ሎሜ/ቶጎ)፣ ማቲዩ ዶሲቪ (ስታንዳርድ ሊየዥ/ቤልጂየም)፣ ፕሪንስ ሰግቢፊያ (ጎዝቴፕ/ቱርክ))፣ ጃኩዌስ ሮማኦ (ኦሎምፒያኮስ/ግሪክ))፣ ላላዊሊ አታኮራ (ሄልሰንበርገ/ስዊድን)፣ አኮት ኢኒንፉል (ካታኮፒያስ/ቆጵሮስ))፣ ኢላስ ቤቦ ((ፎርቹና ዶስልዶርፍ/ጀርመን)

አጥቂዎች

ኢማኑኤል አዲባዮር (ክለብ የለውም)፣ ኮምላን አግበግኒአዳን (ዋፋ/ጋና)፣ ፍሎይድ አይቴ (ፉልሃም/እንግሊዝ)፣ ራዛክ ቦካሪ (ቻቲሮ/ፈረንሳይ)፣ ሰርጌ ጋግፒ (ጄንዋ/ጣሊያን)፣ ፎዶ ላባ (ሬነሳንስ ደ ቤርኬን/ሞሮኮ)

Leave a Reply