የጋቦን 2017 ተሳታፊዎች ፕሮፋይል | ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ [ነብሮቹ]

በቦነስ ክፍያ አለመስማማት ምክንያት ፌድሬሽኑ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተው አድማ እስከመምታት የደረሱት የዲ.ሪ. ኮንጎ ተጨዋቾች በስተመጨረሻም ከስምምነት ደርሰው አፍሪካ ዋንጫውን በተሳካ ሁኔታ ለመጀመር ተዘጋጅተዋል፡፡

ኮንጎ በ2015 የኤኳቶሪያል ጊኒ አፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ የቻለች ሲሆን አሁን ላይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ታልማለች፡፡ በ2015 ከግማሽ ፍፃሜ የወደቁት ነብሮቹ በአሁኑ ግዜ ወጥ አቋም እያሳዩ መሆናቸውን በአፍሪካ ዋንጫው ይሁን በአለም ዋንጫ ማጣሪያው ማሳየት ችለዋል፡፡ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ ወርቃማ ግዜው የነበረው የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን ጠንካራነቱን ያስመሰከረ ሆኗል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት፡ 17

ውጤት፡ ሁለት ግዜ አፍሪካ ቻምፒዮን (1968 እና 1974)

አሰልጣኝ፡ ፍሎረንት ኢቤንጌ

ዲ.ሪ. ኮንጎ በምድብ ሶስት ከካቻምና አሸናፊዋ ኮትዲቯር፣ ቶጎ እና ሞሮኮ ጋር ተደልድላለች፡፡ ኮንጎ በሃገር ውስጥ አሰልጣኝ ከሚመሩት አራት የአፍሪካ ዋንጫው ተሳታፊ ሃገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ አሰልጣኝ ፍሎረንት ኢቤንጌ ከብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው ባሻገር የኪንሻሳውን ሃያል ክለብ ኤኤስ ቪታን ያሰለጥናሉ፡፡ ኢቤንጌ በ2014 ቪታ ክለብ ለካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ሲያደርሱ በ2015 ኮንጎን በአፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን እንድታገኝ አስችለዋል፡፡ ይህ ልምድ ያለው የኪንሻሳ ተወላጅ በዚህም ሳይበቃው ሩዋንዳ ባስተናገደችው ቻን 2016 ሃገሩን የዋንጫ ባለቤት አድርጓል፡፡ ታዲያ የክለብ እና ብሄራዊ ቡድን ሃላፊነትን አጣምሮ የሚመራው ኢቤንጌ ከ2014 ጀምሮ  በስኬት ጎዳና ላይ ይገኛል፡፡ ኮንጎ የ2015ቱ ቡድን ላይ የቻን 2016 አሸናፊ ቡድን ውስጥ የነበሩ ተጫዋቾች አካታለች፡፡ በአለም ዋንጫ ማጣሪ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ የምድቧ መሪ ናት ኮንጎ፡፡ ካላት ወቅታቂ አቋም አንፃር ከምድቧ እንደምታልፍ ብዙዎች ገምተዋል፡፡ በጋቦን ከኮንጎ ልናየው የማንችለው ነገር ቢኖር የአንጋፋው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኪዲያባን አዝናኝ ዳንስ ይሆናል፡፡

ተስፋ

ምርጥ የሆኑ ጨረሽ አጥቂዎችን ኮንጎ ይዛለች፡፡ ከባለፉት 16 ጨዋታዎች ቡድኑ በአማካይ በአንድ ጨዋታ ሁለት ግቦችን ያስቆጥራል፡፡ ይህ ለኮንጎ የጥንካሬዋ መገለጫ ነው፡፡ በጨዋታ ላይ ብዙ ግቦችን ማስቆጠር የሚችል ቡድን እንዳላት በተደጋጋሚ አሳይታለች፡፡ የኢቤንጌው ኮንጎ በጣም ተጭኖ መጫወቱ ግቦችን እንዲያስቆጥር አድርጎታል ይህ ደግሞ በጋቦን ቆይታዋ እጅጉን ይጠቅማታል፡፡ ቡድኑ ከዓመት ዓመት ከመውረድ ይልቅ እየጨመረ እና እየተገነባ መምጣቱ በወጥነት የምድብ ጨዋታዋን ለማድረግ ይረዳታል፡፡ በሃገር ውስጥ የሚጫወቱት ተጫዋቾች እና ከሃገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያላቸው መናበብ አስደናቂ ነው፡፡ ኮንጎ በ2016 የቻን አሸናፊ መሆኑ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነዋል፡፡

ስጋት

ቡድኑ በማጥቃቱ በኩል የተሳካለት ቢሆንም የተከላካይ ክፍሉ በዛው ልክ አሳማኝ አይደለም፡፡ ኮንጎ በውድድሩ ላይ መቆየት ከፈለገች አሰልጣኝ ኢቤንጌ በማጥቃቱ እና በመከላካሉ ላይ ማመጣጠን ይኖርባቸዋል፡፡ የያኒክ ቦላሴ በጉዳት ምክንያት አለመኖር ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ የግራ መስመሩን በሚገባ በመሸፈን አንድ የማጥቃት ምንጭ የነበረው ቦላሴ በተደጋጋሚ ለኮንጎ ወሳኝነቱን አሳይቷል፡፡ የዚህ ልዩነት ፈጣሪ በጉዳት በቡድኑ ውስጥ አለመኖር አሉታዊ ጎን አለው፡፡

የሚጠበቁ ተጫዋቾች

በያኒክ ቦላሴ አለመኖር ምክንያት ሴድሪክ ባካምቦ የማጥቃቱን ሚና ይወጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በስፔን የሚጫወተው ባካምቦ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ወደ ኃላ ተመልሶ አማካዮችን መርዳት ይችላል፡፡ በአለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ሊቢያ ላይ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ባካምቦ ሊታይ የሚገባው ተጫዋች ነው፡፡

ከቻን 2016 አሸናፊው ጆናታን ቦሊንጊም እንደዛው፡፡ ቁመተ ለግላጋው የቲፒ ማዜምቤ አጥቂ ቦሊንጊ በ2016 ስኬታማ የሆነ የውድድር ዘመን ከሃገሩም ከክለቡም ጋር አሳልፏል፡፡ የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙ እንዲሁም ግብ ማስቆጠሩ ላይ ጥሩ መሆኑ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ የኤኤስ ቪታው የግራ ተመላላሽ ጆይስ ሎማሊሳም ከሃገሩ ጋር የቻን ዋንጫን አሸንፏል፡፡ ሎማሊስ በድንቅ ብቃቱ ምክንያት የግሎ ካፍ ሽልማት ላይ የካፍ ምርጥ 11 ላይ መካተት ችሏል፡፡ ዱመርሲ ሞቦካኒ እና ግብ ጠባቂው ማታምፒ ሌሎች መታየት ያለባቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የማጣሪያ ጉዞ

ዲ.ሪ. ኮንጎ በምድብ ሁለት ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊ፣ አንጎላ እና ማዳጋስካር ጋር ነበር የተደለደለችው፡፡ ካደረገቻቸው ስደስት ጨዋታዎች አምስት አሸንፋ በአንድ ተሸንፋ በ15 ነጥብ ምድቡን በበላይነት ጨርሳለች፡፡ 16 ግቦችን ታጋጣሚዎቿ ላይ ስታስቆጥር በአንፃሩ ደግሞ 6 ግቦች አስተናገዳለች፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ንጉምቢ ማታምፒ (ቲፒ ማዜምቤ/ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ጆይል ኪያሱሙቡአ (ዎለን/ስዊዘርላንድ)፣ ሙለፖ ኩዲምባና (አንትወርፕ/ቤልጂየም)

 

ተከላካዮች

ሞፒኮ ኢሳማ (ቲፒ ማዜምቤ/ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ፋብሪስ ሳካላ (አላንያስፖር/ቱርክ)፣ ጆርዳን ኢኮኮ (ገንጎ/ፈረንሳይ)፣ ማርሴል ቲሰራንድ (ኢንጎልስታድ/ጀርመን)፣ ጆይል ሎማሊሳ (ኤኤስ ቪታ ክለብ/ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ጋብሪኤል ዛኩኒ (ኖርዝሃምፕተን/እንግሊዝ)፣ ማንጉሉ ምቤምባ (ኒውካስል ዩናይትድ/እንግሊዝ)

 

አማካዮች

ሄርቬ ኬጅ (ኮርትሬ/ቤልጂየም)፣ የሱፍ ሙሉምቡ (ኖርዊች ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ፖል ሁዜ ምፖኮ (ፓናቲኒያኮስ/ግሪክ)፣ ኒስኪንስ ኬባኖ (ፉልሃም/እንግሊዝ)፣ ሬሚ ሙሉምቡ (አጃክሲዮ/ፈረንሳይ)፣ ምርቬል ቦፔ(ቲፒ ማዜምቤ)፣ ጃኩዌስ ማጎማ (በርሚንግሃም/እንግሊዝ)

አጥቂዎች

ጆናታን ቦሊንጊ (ቲፒ ማዜምቤ/ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ዱመርሲ ሞቦካኒ (ሃል ሲቲ ታይገርስ/እንግሊዝ)፣ ጆርዳን ቦታካ (ቻርልተን አትሌቲክ/እንግሊዝ)፣ ሴድሪክ ባካምቦ (ቪያሪያል/ስፔን)፣ ሎቴቴካ ቦኪላ (አል አሃሊ/ካታር)፣ ፈርመን ሙቤሌ (አል አሃሊ/ካታር)

 

ዲ.ሪ. ኮንጎ በስታደ ኦየም ሞሮኮን ዛሬ ምሽት 4፡00 በመግጠም የምድብ ሶስት ጨዋታዋን የምትጀምር ይሆናል፡፡

Leave a Reply