“አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላይ እምነት አለን ” ታምሩ ታፌ – የሀዋሳ ከተማ ፕሬዝዳንት 

የሁለት ጊዜ የሊግ ቻምፒዮኑ ሀዋሳ ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን አሰከፊ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ ከ10 ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ አስመዝግቦ በደረጃ ሰንጠረዡ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

በክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ታምሩ ታፌ በሰጡት አስተያየት ቡድኑን ለማጠናከር እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“በእንቅስቃሴ ደረጃ በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ ነገር ትልቁ ችግር ግብ ማስቆጠር እንዲሁም ያስቆጠርናቸውን ግቦች አስጠብቀን ያለመውጣታችን ዋጋ እያስከፈለን ስለሆነ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድናችንን ለማጠናከር ቦርዱ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ ስለዚህ ያን ለማድረግ አስበናል፡፡ ” ብለዋል፡፡

ሀዋሳ በሊጉ እያስመዘገበ ያለውን ውጤት ተከትሎ በጫና ውስጥ የሚገኙት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በደጋፊዎችም ተቃውሞ በርክቶባቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የቀድሞው የቡና እና አዳማ አሰልጣኝ ከክለቡ ሊሰናበቱ ይችላሉ ቢባልም ፕሬዝዳንቱ ክለባቸው ከአሰልጣኝ ውበቱ ጎን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

” ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ክለባችን ጥሩ እግርኳስ ይጫወታል፡፡ እኛ አሰልጣኝ ውበቱ አበተን ስናመጣ ባለው ከፍተኛ እውቀት እንደምንጠቀም ስለምናቅ ነው፡፡ ያኔ ላለመውረድ ስንጫወት ውበቱ ታድጎናል ፤  ስለሆነም ውጤት ይጥፋ እንጂ አሰልጣኝ ውበቱ ላይ እምነት ስላለን ለማሰናበት አናስብም፡፡ ለሁላችንም ውበቱ ትልቅ አሰልጣኝ ነው፡፡” ሲሉ ለአሰልጣኙ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከክለቡ ጋር ተያይዘው እየወጡ ባሉ መረጃዎች በቀጣዩ ወር በሚከፈተው የዝውውር መስኮት ተጫዋቾችን   ለማስፈረም ጥረት እያደረገ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተለያየው ዩጋንዳዊው ተከላካይ አይዛክ ኢሴንዴ እና በኤሌክትሪክ ከአሰልጣኝ ብርሀኑ ጋር ባለመስማማት የተለያየው አጥቂ ማናዬ ፋንቱን ለማስፈረም እንቅስቃሴ መጀመሩ ተነግሯል፡፡ በሲዳማ ቡና ያልተሳካ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ናይጄሪያዊው አጥቂ ላኪም ሰኒም ከክለቡ ዝውውር ጋር ስሙ ተነስቷል፡፡ በውድድር አመቱ መጀመርያ ክብረአብ ዳዊትን በሞት ያጣው ሀዋሳ አንድ ግብ ጠባቂ በስብስቡ ላይ ለመጨመር እንደታሰበም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

1 Comment

  1. ሀዋሳ ከነማ ጥሩ ተከላካይ አማካይ ያስፈልገዋል

Leave a Reply