ጋቦን 2017 ፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ ስታሸንፍ የወቅቱ ቻምፒዮን ኮትዲቯር ነጥብ ተጋርታለች

የቶታል 2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሶስት ጨዋታዎች በሰሜን ጋቦን ከተማ ኦየም በሚገኘው ስታደ ኦየም ቀጥለው ተደርገዋል፡፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ ሞሮኮን 1-0 ስታሸንፍ እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎች ባልነበረበት ጨዋታ ቶጎ ከካቻምና አሸናፊዋ ኮትዲቯር ጋር ያለግብ አቻ ተለያይታለች፡፡ እስካሁን በተደረጉት ስደስት ጨዋታዎች አራቱ በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል፡፡

ኮትዲቯር ከቶጎ በተገናኙበት ጨዋታ እምብዛም ማራኪ ያልነበረ እንዲሁም የግብ ማግባት ሙከራዎች ያልታዩበት ሆኖ 0-0 ተጠናቅቋል፡፡ ኮትዲቯር በጆናታን ኮዲጃ እና ሰርጅ ኦሪየር ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡ በተለይ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩ ኦሪየር በግንባሩ የገጨው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ ቶጎ በበኩላ በአንጋፋው አማካይ ማቲዩ ዶሲቪ እና ፎዶ ላባ አማካኝነት የግብ ማግባት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡ ጨዋታውን ብዙ ደጋፊ ወደ ስታዲየም ገብቶ ያልተመለከተው ሆኖ አልፏል፡፡ ውጤቱም የቶጎውን አሰልጣኝ ክላውድ ለርዋን አስደስቷል፡፡ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠው የቶጎው ላላዌሌ አጋሳ ነው፡፡

ዲ.ሪ. ኮንጎ ሞሮኮን 1-0 በሆነ ውጤት በመርታት የምድብ ሶስትን መሪነት ጨብጣለች፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው የመጀመሪያ ቀይ ካርድ በተመዘዘበት ጨዋታ ከቀናት በፊት በቦነስ ክፍያ ጉዳዮች ምክንያት እስከልምምድ ያለመስራት አድማ የደረሱት የኮንጎ ተጫዋቾች በመጀመሪያው አጋማሽ ከረጅም ርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች ተውስነዋል፡፡ የሞሮኮው አማካይ ሙባረክ ቡሶፋ ጨዋታው በተጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራ የሚጠቀስ ነው፡፡ ነብሮቹ በሁለተኛው አጋማሽ የሞሮኮው ግብ ጠባቂ ሙኒር መሃመዲ የሰራውን ስህተት በተጠቀመው ጁኒየር ካባንጋ አማካኝነት ወሳኟን ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ የግራ መስመር ተከላካዮ ጆይል ሎማሊሳ በፈፀመው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወጣ የኮንጎው ማታምፒ የሞሮኮውን አጥቂ የሱፍ ኤል አረቢ የግንባር ኳስ ሊያመክን ችሏል፡፡  የጨዋታው ኮከብ በመሆን የተሸለመው የሞሮኮው አማካይ ሙባረክ ቡሶፋ ነው፡፡

ጨዋታዎቹ ዛሬም ሲቀጥሉ በምድብ አራት ምሽት 1፡00 ላይ ጋና ዩጋንዳን ስትገጥም ምሽት 4፡00 ላይ ማሊ ከግብፅ ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታዎች በፖርት ጀንትል የሚደረጉ ይሆናል፡፡

ፎቶ ምንጭ – ካፍ እና ዴይሊ ሜይል

Leave a Reply