ጋቦን 2017፡ ሴኔጋል ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለች የመጀመሪዋ ሃገር ሁናለች

ስድስተኛ ቀኑን በያዘው የ2017 ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ የምድቡ ሁለት ጨዋታዎች በፍራንስቪል ቀጥለው ተደርገዋል፡፡ የሰሜን አፍሪካ ባላንጣዎቹን ባገናኘው ጨዋታ ቱኒዚያ አልጄሪያ ላይ ወሳኝ ድል ስትቀዳጅ ለቡድኖች ፈተና እየሆነች የመጣችው ሴኔጋል ዚምባቡዌን በቀላሉ ረታለች፡፡

ከፍተኛ ፉክክር እና ጉሽሚያ በነበረበት ጨዋታ ቱኒዚያ ጎረቤቷን አልጄሪያን 2-1 በመርታት ከሽንፈት ማገገም ችላለች፡፡ ከጨዋታው መጀመሪያ ጀምሮ እንደተጠበቀው በፈጣን እንቅስቃሴ ሁለቱም ሃገራት አጥቅተው ለመጫወት ሲጥሩ ታይቷል፡፡ የበረሃ ቀበሮዎቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በያሲን ብራሂሚ እና ኢስላም ሲሊማኒ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርግም የቱኒዚያው ግብ ጠባቂ አይመን ማትሉቲ በድንቅ ሁኔታ አምክኗቸዋል፡፡ ዋሂብ ካዝሪ የካርቴጅ ንስሮቹን ቀዳሚ ሊያደርግ የሚችልበት አጋጣሚን ከቅጣት ምት አግኝቶ የአልጄሪያው ግብ ጠባቂ ማሊክ አስላ አውጥቶበታል፡፡ አህመድ አከያቺም ግብ ማስቆጠር የሚችልበትን እድል በ20ኛው ደቂቃ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ጉዲዮራ እና ማህሬዝ የሞከሯቸውንም ሙከራዎች ማትሉቲ ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን በጠንካራ መከላካል ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁላ ተሸለው የታዩት ቱኒዚያዎች ነበሩ፡፡ የአልጄሪያው የመሃል ተከላካይ አይሳ ማንዲ በራሱ ግብ ላይ በ50ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ መምራት ችለዋል፡፡ ፋውዚ ጉልሃምየመከላከል ድክመቱን ባሳየበት ትዕይንት ካዝሪላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ናይም ሲሊቲ ከመረብ አዋህዶ መሪነቱን ወደ 2 ከፍ አድርጓል፡፡ ግብ ለማግኘት የተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት የበረሃ ቀበሮዎቹ አሰልጣኝ ጆርጅ ሊከንስ ቡድናቸውን የፈለገውን ውጤት ይዞ ባይወጣም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አማካዩ ሶፊያን ሃኒ ልዩነቱን ወደ አንድ ያጠበበትን ግብ የጨዋታው መገባደጃ ላይ አስቆጥል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ በመክፈቻው ጨዋታ በሴኔጋል ሽንፈት የደረሰባት ቱኒዚያ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ስትሆን አልጄሪያ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች፡፡ የቱኒዚዘያው የአጥቂ አማካይ የሱፍ ሳክኒ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ ተመርጧል፡፡

ፈታኝ እየሆነች የመጣችው ሴኔጋል ዚምባቡዌን 2-0 በማሸነፍ ከወዲሁ ሩብ ፍፃሜውን መቀላቀል የቻለች የመጀመሪያዋ ሃገር ሁናለች፡፡ ሁለቱን በሃገር ውስጥ አሰልጣኞች የሚመሩት ሃገራትን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የቴራንጋ አናብስቱ የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ ስፍራ ሲያስቸግሩ አምሽተዋል፡፡

ጦረኞቹ በተደጋጋሚ ከሴኔጋል አጥቂዎች የሚደርስባቸውን ጫና መቋቋም ተስኗቸው በግዜ ሁለት ግብ አስተናግደዋል፡፡ ኬታ ባልዴ ዲያዎ እና ማሜ ቤራም ዲዩፍ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶቹን ቢያመክኑም ልማደኛው ሰይዶ ማኔ ሃገሩን መሪ ያደረገች ግብ በቀላሉ አስቆጥሯል፡፡ ኬታ ባልዴ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት ሄነሪ ሴቬ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የሴኔጋልን መሪነት ወደ 2-0 አስፍቷል፡፡ የዚምባቡዌው ወሳኝ ተጫዋች ካማ ቢሊያት በሴኔጋል አማካዮች የተገደበ እንቅስቃሴን ለማድረግ ተገዷል፡፡

የቴራንጋ አናብስቶቹ በሁለተኛው አጋማሽ ለቁጥር የሚታክቱ የግብ እድሎች ፈጥረው ሲያመክኑ አምሽተዋል፡፡ ጦረኞቹ ይህ ነው የሚባል የረባ እንቅስቃሴ ሳያሳዩ ጨዋታው የተገባደደው፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ዲዩፍ፣ ማኔ፣ ሙሳ ሶ እና ኬታ ባልዴ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶችን ማምከናቸው እንጂ ጨዋታው ከ2-0 በላይ የመጠናቀቅ እድሉ የሰፋ ነበር፡፡ የዚምባቡዌው ግብ ጠባቂ ሙኩሩቫ ያላቀላቸውን ኳሶችን በማዳን ኮከብ ሁኖ አምሽቷል፡፡

በአሊዩ ሲሴ የምትመራው ሴኔጋል አራት ንፁ ግብ ይዛ ሩብ ፍፃሜውን ከወዲሁ መቀላቀል የቻለች ሃገር ሁናለች፡፡ አስፈሪ የአጥቂ መስመር እና የተቀናጀ የተከላካይ መስመር የያዘችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ከውድድሩ አስቀድሞ ለዋንጫ ከተገመቱት ሃገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ የጨዋታው ኮከብ በመሆን የተመረጠው የሴኔጋሉ አምበል ቼክ ኮያቴ ነው፡፡

ጨዋታዎቹ ነገም ሲቀጥሉ በምድብ ሶስት የወቅቱ ቻምፒዮን ኮትዲቯር ዲ.ሪ. ኮንጎን ምሽት 1፡00 ላይ ስትገጥም ሞሮኮ ከቶጎ 4፡00 ላይ ይፋለማሉ፡፡ ጨዋታዎቹ ኦየም በሚገኘው ስታደ ኦየም ይደረጋሉ፡፡

 

የፎቶ ምንጮች – AFP, BackpagePix, EPA

Leave a Reply