ጋቦን 2017፡ ጋና ሩብ ፍፃሜውን ስትቀላቀል ዩጋንዳ ከምድብ ተሰናብታለች

በ2017 የቶታል የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አራት ጨዋታዎች በፓርት ጀንትል ዛሬ ሲደረጉ ጋና ማሊን በመርታት ሩብ ፍፃሜውን ስትቀላቀል ግብፅ ዩጋንዳን አሸንፋለች፡፡ ተሸናፊዋ ዩጋንዳ ከአፍሪካ ዋንጫው በግዜ ተሰናብታለች፡፡

ሁለቱን የምዕራብ አፍሪካ ሃገራትን ያገናኘው የጋና እና ማሊ ጨዋታ በጥቋቁር ከዋክብቶቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡ ጆርዳን አዩ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ወደ አደጋ ክልሉ የላከው ኳስ አሰሞሃ ጂያን አግኝቶ በግንባሩ በመግጨት ጋናን መጀመሪያው አጋማሽ መሪ አድርጓል፡፡ ንስሮቹ በመጀመሪያው 45 እምብዛም ወደ ግብ ሳይደርሱ ቀርተዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽም ኢላማውን የጠበቀ አንድምሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር፡፡ በሁለተኛው 45 ከተጋጣሚያቸው ልቀው ታይተዋል፡፡ ማሊዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጋና ላይ የበላይነትን የወሰዱ ቢሆንም ጠንካራ የነበረውን የጋና የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ አምሽተዋል፡፡ ሙሳ ማሬጋ፣ ሱሌማና ኩሊባሊ እና ሙሳ ዶምቢያ ለማሊ የአቻነት ግብ ለማስገኘት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡ በተለይ ሙሳ ዶምቢያ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ የሞከረው አስደንጋጭ ሙከራ የጋናው ግብ ጠባቂ ብራማ አምክኖበታል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የማሊ ተጫዋቾች የዕለቱን አርቢትር ከበው የፍፁም ቅጣት ምት መነፈጋቸውን ቅሬታ ሲያሰሙ ታይቷል፡፡ የጋናው አማካይ ቶማስ ፓርቴ በካፍ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተምርጧል፡፡ አሰሞሃ ጂያን እና የቡድን አጋሮቹ ከግቧ መቆጠር በኃላ ያሳዩት የደስታ አገላለፅ በብዙዎች ተወዷል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ሁለት ጨዋታ ድል የቀናት ጋና ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለች ሁለተኛዋ ሃገር ሁናለች፡፡ ሴኔጋል ሐሙስ ዕለት ዚምባቡዌን በፍፁም ብልጫ 2-0 ከረታች በኃላ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለች የመጀመሪያዋ ሃገር ነች፡፡ አንድ ነጥብ ያላት ማሊ ከአሁን አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች፡፡

ግብፅ ዩጋንዳን በጨዋታው መገባደጃ ላይ ባስቆጠረችው ግብ ታግዛ 1-0 አሸንፋለች፡፡ የሁለቱ ሃገራት ጨዋታ ተመጣጣኝ የነበረ ሲሆን አልፎ አልፎ ከሚደረጉ የግብ ሙከራዎች ውጪ እምብዛም አስደንጋጭ ሙከራዎች ሳይደረጉበት አልፏል፡፡ በጨዋታው አብዛኛው ክፍለግዜ ክሬንሶቹ ፈርኦኖቹን ተቋቁመው መጫወት ቢችሉም በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠረባቸው ግብ ከምድብ አሰናብቷቸዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገበው የአል አሃሊው ኮከብ አብደላ ኤል-ሰዒድ መሃመድ ሳላህ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ የሰባት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኖቹን ለጣፋጭ ድል አብቅቷል፡፡

ሰዒድ ሳጥኑ ውስጥ አግኝቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ በዩጋንዳው ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኒያንጎ እግሮች መሃል በማለፍ ከመረብ ጋር ተዋህዳለች፡፡ ዩጋንዳ ከ39 ዓመታት በኃላ የተመለሰችበትን የአፍሪካ ዋንጫ በግዜ ተሰናብታለች፡፡ አብዛኞቹ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በአፍሪካ ዋንጫው ከምድብ በቶሎ መሰናበታቸው አሁን አሁን ላይ የለመደ ጉዳይ ሁኗል፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የግብፁ አብደላ ኤል-ሰዒድ ነው፡፡

የአፍረካ ዋንጫው አነጋጋሪ ጉዳዮችን እያሳየ መደረጉን ቀጥሏል፡፡ የመጨዋጫ ሜዳዎቹ ተጫዋቾችን ለጉዳት እየዳረጉ ነው የሚሉ ዘገባዎች በስፋት እየወጡ ሲሆን ዛሬ የማሊ እና ጋና ተጫዋቾች ከጨዋታው አስቀድሞ በፖርት ጀንትል ስታዲየም እንዲያሟሙቁ አልተፈቀደላቸውም ነበር፡፡ የሜዳ ጥራት ችግሮች እንዳሉ ከአፍሪካ ዋንጫው መከፈት በፊት ሞሮኳዊው የካፍ ዋና ፀሃፊ ሂሻም ኤል-ሃምራኒ ማመናቸው የሚታወስ ነው፡፡ የቶጎው ግብ ጠባቂ ኮሲ አጋሳ በሞሮኮው ጨዋታ ባሳየው የወረደ አቋም ምክንያት ሎሜ የሚገኘው ቤቱ በተበሳጩ የቶጎ ደጋፊዎች ጉዳት ደርሶበታል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫው ዕሁድ ሲቀጥል በምድብ አንድ ሩብ ፍፃሜውን የሚቀላቀሉ ሁለት ሃገራት የሚለዩበት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ ጋቦን ከካሜሮን እንዲሁም ጊኒ ቢሳው ከቡርኪና ፋሶ ምሽት 4፡00 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

የፎቶ ምንጮች : AFP, BackpagePix, Filgoal.com

Leave a Reply