ጎንደርን ወደ እግርኳስ ከተማነት የቀየራት ፋሲል ከተማ. . .

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አጼ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ደደቢትን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ በሜዳው ከረጅም ጊዜያት በኋላ ሽንፈት አስመዝግቧል፡፡ በስፍራው የተገኘው የሶከር ኢትዮጵያው ዳንኤል መስፍን ጥንታዊቷ ጎንደር ከተማ ለፋሲል እግርኳስ ክለብ ያላትን ከፍ ያለ ቦታ ታዝቦ ተመልሷል፡፡

ጎንደር ከተማን ለመጀመርያ ጊዜ የሚጎበኝ ሰው ዋንኛ ምክንያቱ ታሪካዊውን የአፄ ፋሲል ቤተ መንግስት ለመመልከት እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን የፋሲል ደጋፊዎች ድርጊት እለቱ የጨዋታ ቀን እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ የቡድኑን ጨዋታ እንዲመለከትና ልዩ ትዝታ ይዞ እንዲመለስም ምክንያት ይሆነዋል፡፡ በርካታ ቱሪስቶች ከፋሲል ቤተ-መንግስት ድንቅ ኪነ-ህንፃ ባሻገር የከተማው ህዝብ ለክለቡ ባለው ጥልቅ ፍቅር ይገረማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ጎንደር ታሪካዊ ብቻ ሳትሆን ጥልቅ የእግርኳስ ፍቅር ያሳበዳት ከተማም ጭምር እንደሆነች ይገልጻሉ፡፡

ዕለቱ የትኛውም ቀን ቢሆን ፋሲል ጨዋታ የሚኖረው ከሆነ ከማለዳው አንስቶ የጎንደር ከተማ ጎዳና እና ዋና ዋና አደባባዮች በክለቡ ቀይ እና ነጭ መለያ ያሸበርቃሉ፡፡  በእምነት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር በርከታ ሰዎች ቀይ እና ነጭ የክለቡን ማልያ ለብሰው ሲቀሳቀሱ መመልከት በጎንደር ከተማ የእለት ተእለት ልማድ ቢሆንም ለከተማው እንግዳ ለሆኑ ግለሰቦች ግን አግርሞትን የሚያጭር ነው፡፡ ሆቴሎች ፣ ካፌዎች ፣ ተቋማት እና የንግድ ሱቆች ከጠዋት ጀምሮ የፋሲልን ባንዲራ ከፍ አድርገው ሲሰቅሉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡  የከተማዋ ዋንኛ የትራንስፖርት መገልገያ የሆኑት ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎች የክለቡን አርማ ሰቅለው ሲመላለሱ ትመለከላችሁ፡፡

በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የልብስ መሸጫ ሱቆች ውስጥ በተለያየ ዲዛይን የተሰሩና የክለቡን አርማ የያዙ ማልያዎች ፣ ስካርፎች እና ቲሸርቶች በቀላሉ ይገኛሉ፡፡ ህዝቡም ከክለቡ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ነገሮች ለመግዛት እንደማያመነታ በፋሲለደስ ስታድየም የሚታደመውን ደጋፊ መመልከት በቂ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ የስታድየሙ መቀመጫዎች የክለቡን ነጭ እና ቀይ መለያ ባጠለቁ ደጋፊዎች የተሞላ ነው፡፡

ፋሲል ከተማ ለረጅም ዘመናት በሀገሪቱ ትልቅ የሊግ እርከን መወዳደር ባይችልም የህዝቡን ልብ ከማግኘት ያገደው የለም፡፡ በተለምዶ ደጋፊ ሲባል ከምናስበው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በተለየ መልኩ በእድሜ የገፉ አረጋውያን ፣ የእምነት አባቶች ፣ ቱሪስቶች ፣ የመንግስት ሹመኞች ፣ ህፃናት እና ሴቶች ፋሲልን በስታድየም ተገኝተው በጋለ ስሜት ከመደገፍ ተቆጥበው አያውቁም፡፡ ከደደቢት ጋር በተደረገው ጨዋታ የከተማው ከንቲባ የክለቡን መዝሙር በመዘመር ጨዋታውን ሲያስጀምሩ መመልከትም ፋሲል ለህዝቡ ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ገላጭ ነው፡፡

በአፄ ፋሲለደስ ስታድየም ከሚታየው ልዩ የደጋፊ ድባብ ባሻገር የባህል ተወዛዋዦች በክለቡ መለያ አሸብርቀው የሚያሳዩት ትርኢት በኢትዮጵያ ያልተለመደና አስደናቂ ነው፡፡ ስታድየሙ ከአፍ እስከ ገደፍ በተመልካች የሚሞላ በመሆኑ ከሜዳው ውጪ በሚገኝ ተራራ ላይ ተቀምጠው የክለቡን ጨዋታ የሚከታተሉ ደጋፊዎች ቁጥርም ጥቂት የማይባል ነው፡፡

ስታድየሙ ለቁጥጥር አስቸጋሪ በሚባል ሁኔታ በተመልካች ቢሞላም የጸጥታ ኃይሎች ቁጥር ግን ጥቂት ነው፡፡ ይልቁንም ከ200 በላይ የሚሆኑ የክለቡ ደጋፊዎች የተለየ መለያ በመልበስ የስታድየሙም ደህንነት በመጠበቅና በማስተባበር ዋናውን ተግባር ሲፈጽሙ ተስተውሏል፡፡ ይህ የፋሲል ደጋፊዎች ተግባር በሃገራችን በርካታ ህዝብ በሚታደምባቸው ጨዋታዎች ላይም ቢለመድ በኢትዮጵያ እግርኳስ አሳሳቢ ከሆኑ ጉዳዮች እንዱ የሆነው ስርአት አልበኝነትን ለመቆጣጠር አስዋፅኦ ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡

በአጠቃላይ ለወትሮውም በህዝቡ በጥልቅ ፍቅር የሚወደደው ፋሲል ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ተከትሎ በከተማው የሚታየው ድባብ ጎንደርን ‘የእግርኳስ ከተማ’ አስመስሏታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *