ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 ጅማ አባ ቡና | የአሰልጣኞች አስተያየት 

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባ ቡናን በአዲስ አበባ ስታድየም አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች ለጋዜጠኞች የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል።


ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

” ጨዋታውን አቻ በመውጣታችን ደስ አላለንም። የመጀመሪያው እና ሁለተኛው አጋማሽ የተለያየ መልክ ነበረው። በመጀመሪያው 45 ለተጋጣሚያችን በቂ እድል ሰጥተን ነበር። እኛም በምናስበው መንገድ የጎል እድል አልፈጠርንም። በሁለተኛ አጋማሽ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ተጫዎቾቻችን የተሻለ ጥረት አድርገዋል። ግብ አግብተናል ፤ የጎል እድሎችንም አምክነናል። ነገር ግን በኛ ደረጃ ተጫውተናል ብዬ አላስብም። ምክንያቱን እንዲህ ነው ብዬ መናገር ባልችልም ያው ከስህተታችን መማር ነው። አንዳንዴ ትልልቅ ቡድኖች እንደዚህ አይነት ችግር ያጋጥማቸዋል። ያንን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው ። ቡድናችን የሚጠበቅበት ብቃት ላይ እንዲደርስ ጠንክረን እየሰራን ነው ። ”

ለተጋጣሚ ቡድን ስለሰጡት ግምት

” እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው የኖርኩት። ለማንም ቡድን ቀላል ግምት ሰጥተን አናውቅም። ቡድኖች ሁሉ ለኛ አንድ ናቸው። ቻምፒዮን ለመሆን እያንዳንዱ ሶስት ነጥብ አስፈላጊያችን ነው።”

ስለደጋፊዎች ተቃውሞ

” ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው ፤ ደጋፊዎችም ማሸነፍ ለምደዋል። ከስቴድየም ጨፍረው መውጣት ነው የለመዱት ። እና ቡድኑ ጥሩ አልጫወት ሲል መቃወማቸው የተለመደ ነው። አሰልጣኞችን ጠልተው ነው ብዬ አላስብም። ቡድኑ ሜዳ ላይ በሚጠበቅበት መንገድ አልጫወት ሲል ደጋፊዎች ይቃወማሉ ። ይሄ በየትኛውም አለም ያለ ነው። ደጋፊዎቻችን ቀኝ እጆቻችን ናቸው ብለን ነው የምናስበው። እናም እስካላሸነፍን እና ጥሩ እስካልተጫወትን ድረስ ከትልቅ  ቡድን ደጋፊዎች የሚጠበቅ ነው። ተቃውሞው ተፅእኖ ይኖረዋል ፤ ግን ይህ የእግር ኳስ ባህሪ ነው። ”

ስለቀጣይ ጨዋታዎች

ሁልጊዜም ጨዋታዎችን አሸንፈን ደጋፊዎቻችን ከሜዳ ተደስተው ቢወጡ ደስታችን ነው ። አንዳንድ ቀን አይሳካም ። በሰሞኑ ጨዋታዎች ቡድናችን ጥሩ እየተንቀሳቀሰ አይደለም ። የተጎዱብን ተጨዋቾችም አሉ ፤ ግን ምክንያት ለመስጠት ፈልጌ አይደለም ። ጠንክረን ሰርተን ደጋፊዎች የሚፈልጉትን ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ እንደምናሳያቸው እርግጠኛ ነኝ።

ደረጄ በላይ – ጅማ አባ ቡና

ስለጨዋታው

” ጨዋታው አሪፍ ነበር ፤ በርግጠኝነት ማሸነፍ ይገባን ነበር። ምክንያቱም የተሻለ የጎል እድል የፈጠርነው እኛ ነን። ግን ጊዮርጊስ የምናከብረው ክለብ ነው ። ትንሽ የተጨናነቁ ይመስሉ ነበር ፤ እኛ ካለ ጫና በመጫወታችን የተሻለ ነገር ሰርተን ልንወጣ ችለናል። ”

” ዛሬ ለየት የሚያረገው ነገር አሁን ከክለቡ ጋር ልለያይ መሆኑ ነው። አሁን ያያችኀቸው ልጆች በጣም እየተጨናነቁ ነበር ሜዳቸው ላይ የሚጫወቱት ። ምክንያቱም ይሰደቡ ነበር። ስለዚህ ዛሬ ያስገባሁዋቸው በአብዛኛው ክለቡን ይዘውት የወጡትን ተጨዋቾች ብቻ ነው። እንደሚችሉ ማሳየት እንዳለባቸው ነገርኳቸው። ያው እንደሚችሉም አይታችኋቸዋል። በዛሬው ጨዋታ ተጨዋቾቼም ታክቲካሊ ድሲፕሊንድ ነበሩ። እጅግ በጣም ጥሩ ነበሩ ። እንደምታውቁት በጣም ትንንሽ ልጆች ናቸው። ስድስት የሚሆኑት ለወጣት ብሔራዊ ቡድን የተጫወቱ ናቸው ።”



” ክለቡ ውስጥ መስራት ስላልቻልኩ እና ነፃነት ስላጣው ከሀላፊዎቹ ጋር ተነጋግረን ከክለቡ ለመለያየት ጫፍ ላይ ደርሻለው። ለጅማ አባ ቡናም መልካም እድል እመኛለው ” ያሉት አሰልጣኙ በዚህ እና በክለቡ ዙሪያ ባሉ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፊ መግለጫ ሰጥተዋል። የመግለጫውን ሙሉ ቃልም ነገ ከረፋዱ 5፡00 ላይ በአባይ ኤፍ ኤም 102.9 በሚኖረን የሬድዮ ፕሮግራም እንደምናሰማችሁ እየገለፅን በድረገፃችን ላይም በፅሁፍ ወደናንተ እንደምናደርስ ቃል እንገባለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *