የ2017 የቶታል የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጇ ጋቦን እና ጊኒ ቢሳው ከምድብ የተሰናበቱበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው የፊፋ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ለሁለተኛ ግዜ የምድብ ጨዋታን እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ መምራት ችሏል፡፡
ሊበርቪል ላይ በተካሄደ ጨዋታ ጋቦን ከካሜሮን ጋር ያለግብ አቻ ተለያይታ ከአፍሪካ ዋንጫው ተሰናብታለች፡፡ ጋቦን የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅታ ከምድብ ማለፍ የተሳናት አራተኛዋ ሃገር ሁናለች፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ (1976)፣ ኮትዲቯር (1984) እና ቱኒዚያ (1994) አዘጋጅ ሆነው ከምድብ የተሰናበቱ ሃገራት ናቸው፡፡ በጨዋታው ጥቋቁር ግስላዎቹ በመጀመሪያው ደቂቃ እና መገባደጃው አከባቢ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በተለይ የጨዋታው መገባደጃ ላይ ዴኒስ ቦአንጋ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡ አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ ዲዲዬ ንዶንግ ሞክሮ የካሜሮን ወጣቱ ግብ ጠባቂ ፋብሪስ ኦንዳ በድንቅ ሁኔታ አምክኖበታል፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የጋቦኑ አማካይ ዴኒስ ባአንጋ ነው፡፡
ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በመራው ጨዋታ ቡርኪናፋሶ ጊኒ ቢሳውን ፍራንስቪል ላይ 2-0 በማሸነፍ ምድቡን በመሪነት ጨርሳለች፡፡ ሩድኒልሰን ሲልቫ በራሱ ግብ ላይ በግንባር በመግጨት አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን መሪ አድርጓል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ጊኒ ቢሳው በኳስ ቁጥጥር የተሻለ የነበሩ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም፡፡ በርትራንድ ትራኦሬ በ57ኛው ደቂቃ ሌላ ግብ አስቆጥሮ ቡርኪናፋሶ ከምድቧ አልፋለች፡፡ የፈረሰኞቹ ፕሪጁስ ናኮልማ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ ተመርጧል፡፡
የምድብ ሁለት አላፊ አንድ ሃገር ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚለይ ይሆናል፡፡ አስቀድማ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለችው ሴኔጋል አልጄሪያን ስትገጥም ዚምባቡዌ ከቱኒዚያ ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታዎች ምሽት 4፡00 ይጀምራሉ፡፡