ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ በምድብ ለ መሪነት 1ኛውን ዙር አጠናቋል 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ 9ኛ ሳምንት (የ1ኛ ዙር የመጨረሻ ሳምንት) ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች ተገባዷል፡፡

እሁድ እና ዛሬ በተደረጉት የ9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ አርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ሲያሸንፉ ጌዲኦ ዲላ ያልተጠበቀ ድል አስመዝግቧል፡፡

እሁድ 09:00 ይርጋለም ላይ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና ልደታ ክፍለ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በተመሳሳይ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ጌዲኦ ዲላን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ በውድድር ዘመኑ በንግድ ባንክ ብቻ ተሸንፎ ሌሎቹን በማሸነፍ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው ሀዋሳ በጌዲኦ ዲላ መሸነፉ ያልተጠበቀ ነበር፡፡

ቀሪዎቹ ጨዋታዎች ዛሬ የተደረጉ ሲሆን አበበ ቢቂላ ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ከድንቅ እንቅስቃሴ ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስን 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ አስናቀች ቲቤሶ ግብ ከማስቆጠሯ በተጨማሪ ድንቅ እንቅስቃሴ ስታሳይ ቅድስት ቦጋለም የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመምራት ድንቅ ሆና ውላለች፡፡ የአሰልጣኝ አስራት አባተ አአ ከተማም በሒደት ወደ ውድድር ሪትም እየገባ እንደሆነ ያሳየበትን እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል፡፡

በተመሳሳይ 09:00 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-0 በማሸነፍ በምድብ ለ መሪነት አንደኛውን ዙር አጠናቋል፡፡ ለንግድ ባንክ ትግስት ያደታ ፣ አዲስ ጌታቸው እና ቤቴልሔም ታምሩ ሲያስቆጥሩ ትግስት ያደታ ጎል ከማስቆጠሯ በተጨማሪ መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ችላለች፡፡  ነገር ግን ንግድ ባንክ አሁንም የወሳኝ ተጫዋቾቹ ሽታዬ እና ረሂማን አግልግሎት አለማግኘቱ ቡድኑ በማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ የነበረውን ጥንካሬ እንዲያጣ አድርጓታል፡፡ የቅድስት ማርያሟ ኮከብ መዲና አወል በእንቅስቃሴዋ የተመልካችን ቀልብ መግዛት ብትችልም ከቡድን አጋሮቿ ጋር የምታደርገው እንቅስቃሴ መልካም ባልመሆኑ ቡድኑን ዋጋ ስታስከፍለው ተስተውሏል፡፡

የሳምንቱ ከፍተኛ ውጤት በተመዘገበበት የ11:30 ጨዋታ ደግሞ አርባምንጭ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማን 4-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ አርባምንጮች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ቀድመው ጎል በማስቆጠር የጨዋታ ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን ልደት ቶሎአ በጨዋታው ሁለት ጎል በማስቆጠር እና ድንቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ለቡድኑ ውጤታማነት ከፍተኛውን ሚና ተጫውታለች፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ 1ኛው ዙር ተስተካካይ ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ ጥር 29 ይጠናቀቃል፡፡ ዘግይተው ወደ ውድድር የገቡት ሲዳማ ቡና እና አአ ከተማም በመጀመርያዎቹ 3 ሳምንታት ያመለጧቸውን ጨዋታዎች የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

የምድብ ለ ሰንጠረዥ

ተስተካካይ ጨዋታዎች

እሁድ ጥር 21 ቀን 2009

09:00 አርባምንጭ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ (አርባምንጭ)

ሀሙስ ጥር 25 ቀን 2009

09:00 አቃቂ ቃሊቲ ከ ሲዳማ ቡና (አአ ስታድየም)

11:30 አዲስ አበባ ከተማ ከ ጌዲኦ ዲላ (አአ ስታድየም)

ሰኞ ጥር 29 ቀን 2009

09:00 ሲዳማ ቡና ከ አዲስ አበባ ከተማ (ይርጋለም)

የምድብ ሀ 1ኛው ዙር ባለፈው ሳምንት ሙሉ 30 ነጥቦች በሰበሰበው ደደቢት መሪነት ተጠናቋል፡፡

የምድብ ሀ ሰንጠረዥ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *