ሲዳማ ቡና የኬንያው አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳን ውል እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ድረስ ማራዘሙን አረጋግጧል፡፡
በ2006 የውድድር ዘመን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሲዳማ ቡናን ሲያገለግል የቆየው ኬኒያዊው አንጋፋ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ ውሉ ባሳለፍነው ታህሳስ መጨረሻ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ በዚህም ምክንያት ያለፉትን 3 ጨዋታዎች መሰለፍ ሳይችል ቆይቶም ነበር፡፡
የኤሪክ የውል እድሳት ሙሉ ለሙሉ በመጠናቀቁ ሲዳማ ቡና በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀሙስ አርባምንጭ ላይ ከአርባምንጭ ከተማ ለሚያደርገው ጨዋታ ከቡድኑ ጋር አብሮ ተጉዟል፡፡
በተያያዘ የክለቡ ዜና ሲዳማ ቡና ለሁለት አመት እግዳ ባስተላለፈበት አጥቂ በረከት አዲሱ ምትክ ጋቦናዊ አጥቂ በማምጣት ሙከራ ላይ እንደሆነ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ መንግስቱ ሳሳሞ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡