ጋቦን 2017፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ እና ሞሮኮ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቀሉ

​የራሺድ አሉዊ ድንቅ ግብ የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮኗን ኮትዲቯርን ከውድድር ሲያስወጣ ዲ.ሪ. ኮንጎ ምድብ 3ን በመሪነት የጨረሰችበትን ድል ቶጎ ላይ ተቀዳጅታለች፡፡

ሞሮኮ ኮትዲቯርን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ የሩብ ፍፃሜ ተፋላሚነቷን አረጋግጣለች፡፡ ኮትዲቯርን በ2015 ለአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊነት ያበቃት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ አሁን ደግሞ የአትላስ አንበሶቹን ከአስቸጋሪው ምድብ ማሳለፍ ችሏል፡፡ በኳስ ቁጥጥር ዝሆኖቹ የተሻሉ ቢሆንም የግብ ማግባት ችግሮች ያሉበት ቡድኑ ከመውደቅ ሊተርፍ አልቻለም፡፡ ለማለፍ አንድ ነጥብ ብቻ በቂዋ የነበረው ሞሮኮ ከጨዋታው መጀመሪያ አንስቶ በተደራጀ መከላከልን እና መልሶ ማጥቃት ተጋጣሚዋን ፈትናለች፡፡ በሞሮኮ በኩል ፈይሰል ፋጅር የመታው ቅጣት ምት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሲሆን ሰለሞን ካሉ እና ዌልፍሬድ ዘሃ ለኮትዲቯር ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድረገዋል፡፡ ራሺድ አሉዊ በግሩም ሁኔታ ከሳጥኑ ውጪ ያስቆጠረው ግብ ሞሮኮን ለድል አብቅቷል፡፡ ሰለሞን ካሉ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ ተመርጧል።

ግብ ለማስቆጠር ሲቸገር የማይስተዋለው በፍሎረንት ኢቤንጌ የሚመራው ዲ.ሪ. ኮንጎ ቶጎን 3-1 አሸንፏል፡፡ ቶጎ የመጀመሪያ ተመራጭ ግብ ጠባቂዋን ኮሲ አጋሳን በሲድሪክ ሜንሳ ቀይራ ወደ ሜዳ ብትገባም ከሽንፈት አላመለጠችም፡፡ አጋሳ በቶጎ ደጋፊዎች ቡድኑ በሞሮኮ 3-1 መሸነፉን ተከትሎ ሎሜ የሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህን ተከትሎ ተጫዋቹ ወደ ሃገሩ እንዲመለስ ፌድሬሽኑ ከመጨረሻው የምድብ ጨዋታ በፊት ፈቅዶለታል፡፡ ጁኒየር ካባናንጋ የአፍሪካ ዋንጫውን ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት መምራት የቻለበትን ግብ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያስቆጥር ንዶምቤ ሙቤሌ የነብሮቹን ሁለተኛ ግብ በሜንሳ አናት ላይ ኳስን በመስደድ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ቶጎ በፎዶ ላባ ግብ ልዩነቱን ቢየጠቡም ፖል ሆዜ ፖኩ በቅጣት ምት ሶስተኛውን ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ቶጎ በመጨዋታው መገባደጃ በኤማኑኤል አዲባዮር ግብ ለማስቆጠር ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ሶስት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ጁኒየር ካባናንጋ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡

ምድቡን ዲ.ሪ. ኮንጎ በ7 ነጥብ በላይነት ስታጠናቅቅ ሞሮኮ በ6 ነጥብ ሁለተኛ ሁኗ ከምድብ ሶስት ማለፍ ችላለች፡፡ ለዋንጫው ከተገመቱት ሃገራት መካከል ኮትዲቯር እና አልጄሪያ ሳይጠበቅ ከምድብ ተሰናብተዋል፡፡ አልጄሪያ ከአፍሪካ ዋንጫው ውጪ መሆኗን ተከትሎ ቤልጂየማዊው የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጆርጅ ሊከንስ ከስራ ገበታቸው በራሳቸው ፍቃድ ተነስተዋል፡፡ ሊክንስ ከሶስት ወራት በፊት የክሮሺያዊውን ሚሎቫን ራይቫክ ስንብት ተከትሎ ነው ወደ አልጄሪያ አሰልጣኝነት የመጡት፡፡ 

የምድብ አራት ጨዋታዎች እረቡ ሲደረጉ አስቀድማ ማለፏን ያረጋገጠችው ጋና ግብፅን ስትገጥም ከምድቡ የተሰናበተችው ዩጋንዳ ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ ካለችው ማሊ ጋር ትጫወታለች፡፡ ጨዋታዎቹ ምሽት 4፡00 ይጀምራሉ፡፡    

የፎቶ ምንጭ : AFP

Leave a Reply