የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር ከተጀመረ የ4 ሳምንታት እድሜን አስቆጥሯል፡፡ ከደደቢት እና ሀዋሳ ከነማ ጨዋታ ውጪም ሌሎቹ የ4 ሳምንታት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም እንደተለመደው የዚህን ወር ኮከቦች መርጣለች፡፡

ባለፉት ወራት ተቆጣጥረውት የነበሩት የክልል ክለብ ተጫዋቾች በዚህ ወር እምብዛም ያላንፀባረቁ ሲሆን በዚህ ወር ድንቅ አቋማቸውን ያሳዩት የመከላከያ እና ንግድ ባንክ ተጫዋቾች ወሩን ተቆጣጥረውታል፡፡

 

ግብ ጠባቂ – ሮበርት ኦዶንግካራ

ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ በርቀት የሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ ቢሆንም ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ አንፃር የሊጉ አጥቂዎች ሲፈትኑት አይታይም፡፡ ባለፉት ጠቂት ጨዋታዎች የተስተዋለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነበር፡፡ ከአዳማ ከነማ ፣ ወላይታ ድቻ እና መከላከያ ጋር በተደረጉት ጨዋታዎች ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ያዳነ ሲሆን ትኩረቱ ፣ ቦታ አጠባበቁ እና ቅልጥፍናው ለሊጉ ግብ ጠባቂዎች ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ የባንኩ ዳዊት አሰፋ ፣ የወልድያው ሲሳይ ባንጫ እና የዳሽኑ ደረጄ አለሙ ሌሎች የሚጠቀሱ ግብ ጠባቂዎች ናቸው፡፡

ተከላካዮች

ሲሳይ ደምሴ

የመከላከያው ተከላካይ ወጥ አቋሙን በማሳየት መከላከያን ወደ ቻምፒዮንነት ፉክክሩ አስጠግቶታል፡፡ ሲሳይ ከድንቅ ተከላካይነቱ ባሻገር ቡድን የመምራት ችሎታውን ሚካኤል ደስታ ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች አምበል በመሆንም አሳይቷል፡፡ ከቡድን ጓደኛው ተስፋዬ በቀለ ጋር የፈጠሩት ጥምረትም በሊጉ ከሚገኙ ድንቅ የተከላካይ ክፍል ጥምረቶች አንዱ ሆኗል፡፡

ቢንያም ሲራጅ

የንግድ ባንኩ ተከላካይ ብስለት አስገራሚ ነው፡፡ በዚህ ወር ንግድ ባንክ ከ4 ጨዋታ የተቆጠረበት ግብ አንድ ብቻ ሲሆን ለዚህም የቀድሞ የሐረር ሲቲ ተከላካይ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡

አይናለም ኃይለ

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ ዳሽንን በአምበልነት እየመራ ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው የሚወጡበትን የተከላከይ መስመር ጥንካሬ ፈጥሯል፡፡ በሁለተኛው ዙር ዳሽን ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ሶስቱን አቻ የተለያየውም በአይናለም እና ጓደኞቹ ብርታት ነው፡፡ የወላይታ ድቻው ኃይለየሱስ ትዛዙ እና የንግድ ባንኩ አቤል አበበ ሌሎች ተጠቃሽ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

 

አማካዮች

ታዲዮስ ወልዴ

የባንኩ አምበል በሊጉ ካሉ ጥሩ የታክቲክ ግንዛቤ ካለቸው አማካዮች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ የቀድሞው የድሬዳዋ ከነማ አማካይ በባንክ የአማካይ ክፍል ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር ተጣምሮ ወጥ አቋሙን አሳይቷል፡፡ በተክለሰውነቱ ግዙፍ ባይባልም በታታሪነት የባንክን የኋላ መስመር ከለላ ሲሰጥ ድንቅ ነው፡፡

ተክለወልድ ፍቃዱ

በዚህ ወር መከላከያ ላሳየው መሻሻል ተጠቃሽ ተጫዋች ነው፡፡ ተክለወልድ ከዳሽን ቢራ ጋር በተደረገው ጨዋታ ከውድድር ዘመኑ ድንቅ አቋሞች አንዱን አሳይቶናል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤሌክትሪክ ጋርም የጨዋታው ኮከብ የሚያስብል ድንቅ አቋም አሳይቷል፡፡

ደረጄ መንግስቱ

የንግድ ባንኩ አማካይ ከተደበቀበት ወጥቷል፡፡ በአንደኛው ዙር እምብዛም ጨዋታዎች ላይ ያልተሰለፈው ደረጄ በሁለተኛው ዙር ንግድ ባንክ ላሳየው የበላይነት ከታዲዮስ ጋር የፈጠረው ጥምረት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሳጥን ሳጥን የሚያደርገው ሩጫ እና ቦታ አጠባበቁ (በተለይ በማጥቃት አጨዋወት ላይ) ድንቅ ነው፡፡

ታፈሰ ሰለሞን

የአጭሩ አማካይ ተሰጥኦ የማያከራክር ቢሆንም በጨዋታ ላይ ሲደበቅ እና ወጥ አቋም ማሳየት ሲሳነው ቆይቷል፡፡ በዚህ ወር ከሶስት ጨዋታ 7 ነጥቦችን የሰበሰበው ሀዋሳ ከነማ የግብ እድሎች የሚመነጩት ከቀድሞው የኒያላ ኮከብ ነው፡፡

 

አጥቂዎች

ፊሊፕ ዳውዚ

አንዴ ቀዝቀዝ ሌላ ጊዜ ጎላ ብሎ የሚታየው ፊሊፕ ዳውዚ በዚህ ወር ወጥ አቋሙን አበርክቷል፡፡ በ4 ጨዋታዎች 5 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

ባዬ ገዛኸኝ

ባዬ በድጋሚ ዝርዝር ውስጥ ገብቷል፡፡ የድቻው አጥቂ ጎንደር ላይ 3 ነጥብ ይዘው እንዲመለሱ ድንቅ አቋሙን ያበረከተ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ጋር በተደረጉ ጨዋታዎችም ግቦች አስቆጥሯል፡፡

ኤሪክ ሙራንዳ

ኬንያዊው ግዙፍ አጥቂ ሲዳማ ቡና በመሪነት እንዲቆይ በዚህ ወር ድንቅ ግልጋሎት አበርክቷል፡፡ ጎንደር ላይ አንድ ነጥብ ሲያገኙ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን አርባምንጭን ሲያሸንፉም ግብ አስቆጥሯል፡፡ አሁን ኤሪክ የሲዳማ ቡና ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኗል፡፡ የሀዋሳ ከነማው ተመስገን ተክሌ ሌላው በዚህ ወር የሚጠቀስ አጥቂ ነው፡፡

 

የመጋቢት ወር ኮከብ ተጫዋች – ተክለወልድ ፍቃዱ

ተክለወልድን የመሰለ ድንቅ አማካይ በድንገት ማጣት እጅግ ያስደነግጣል፡፡ እጅግ ድንቅ በሚባል አቋም ላይ የነበረ ሲሆን ማንኛውም በቅብብል ላይ የተመሰረተ እግርኳስን መጫወት ለሚፈልግ ቡድን የተክለወልድ አይነት ተጫዋች ያስፈልገዋል፡፡ የቡድኑን የኳስ ፍሰት ሲቆጣጠር ፣ በድንቅ የኳስ ክህሎት ተጫዋቾችን ሲያልፍ እና ቁልፍ ኳሶችን ለአጥቂዎች ሲያደርስ የምናውቀውን ተክለወልድ በሞት መነጠቅ በእርግጥም ኪሳራ ነው፡፡

የመጋቢት ወር ኮከብ አሰልጣኝ – ፀጋዬ ኪዳነማርያም

አሰልጣኝ ፀጋዬ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ የተናገሩትን ተግብረዋል፡፡ በትኩረት ማጣት በሚቆጠሩ ግቦች የሚገባውን ነጥብ መሰብሰብ ያልቻለው ባንክ አሁን ተጋጣሚዎች አሳምኖ ማሸነፍ ጀምሯል፡፡ በዚህ ወር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ በድል ላጠናቀቀው ንግድ ባንክ ከፍተኛ መሻሻል አሰልጣኙ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ውበቱ አባተ ፣ ዘላለም ሽፈራው እና ገብረመድን ኃይሌ ሌሎች የሚጠቀሱ አሰልጣኞች ናቸው፡፡

ያጋሩ