የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወላይታ ድቻ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጀምር በአዲስ አበባ ስቴድየም ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡

ጨዋታው ግሩም ጎሎች በተሰተናገዱበት እና ጠንካራ የመሸናነፍ ፍላጎት እንዲሁም ማራኪ  እንቅስቃሴ የታየበት ሆኖ አልፏል፡፡ የዕለቱ ዳኛ የጨዋታውን መጀመር ፊሽካ ካሰሙበት ቅፅበት ጀምሮ እንግዶቹ ወላይታ ድቻዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደጎል መድረስ ችለዋል፡፡ ጥረታቸው በጊዜ ሰምሮ ግብ ለማስቆጠርም የቅፅበት ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ ገና በ1ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አላዛር ፋሲካ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ድቻን መሪ አድርጓል፡፡

ባለሜዳዎቹ ንግድ ባንኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የፈጀባቸው ደቂቃ አነስተኛ ነበር፡፡ 6ኛው ደቂቃ አቤል አበበ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ነፃ በሆነ አቋቋም ላይ የተገኘው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ወደ ግብነት ቀይሮ ንግድ ባንክን አቻ አድርጓል፡፡
ጨዋታው በፈጣን እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል ማራኪ የኳስ ፍሰት መታየት ችሏል፡፡ በተለይም ድቻዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው በ12ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሃኑ ፣ 28ኛው እና 34ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በአላዛር ፋሲካ አማካኝነት ጠንካራ የግብ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻሉም፡፡ በአንፃሩ  ባለሜዳዎቹ ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ በሚፈጥሩት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ሰምሮላቸው 43ኛው ደቂቃ ላይ በቢንያም በላይ አማካኝነት መሪ የምታደርጋቸውን ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በንግድ ባንክ 2-1 መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ እስከ 65ኛው ደቂቃ ድረስ ተመጣጣኝ የሆነ  ፉክክር በሁለቱም በኩል ቢታይም የጨዋታው ደቂቃ በገፋ ቁጥር ውጤት ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ወደኋላ ያፈገፈጉት ንግድ ባንኮች ሙሉ ለሙሉ በእንግዶቹ ቡድን ብልጫ  ተወስዶባቸዋል፡፡

ወላይታ ድቻዎች ምንም እንኳ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ቢሆኑም የሚባል የማግባት እድል በቀሩት ደቂቃዎች መፍጠር ላይ ሲቸገሩ ተስተውለዋል፡፡ ሆኖም በመጨረሻ የአቻነት ጎል ፍለጋ የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶላቸው 83ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ በቀኝ መስመር ላይ ጥሩ የማጥቃት አማራጭ ሲፈጥር የነበረው ፀጋዬ ብርሀኑ ያሻማውን ኳስ በዛብህ መለዮ በግራ እግሩ ደገፍ በማድረግ ወላይታ ድቻን አቻ ማድረግ ችሏል ።

በቀሩት ጥቂት ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድል ለማስመዝገብ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ወጣት ተጫዋቾችን የጨዋታው አካል ማድረጋቸው ለተመልካች ጥሩ የሆነ እግርኳስ እንድንመለከት አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

Leave a Reply