​አዲስ አበባ ከተማ 0-1 ኢትዮጵያ ቡና | የአሰልጣኞች አስተያየት

ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው

“ጥሩ ጨዋታ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ ቀላል ቡድን አይደለም ፤ ኳስን ይዞ መጫወት የሚችል ጥሩ ቡድን ነው። መልካም እንቅስቃሴ በጨዋታው ተመልክተናል። ያደረግናቸው የተጫዋች ለውጦች ጨዋታውን ቀይረውታል ብዬ አስባለሁ።”

አህመድ ረሺድ ከጉዳት መልስ

“አህመድ ረሺድ ወደ ጨዋታው እንዲገባ ያደረግነው ሙሉ ጤነኛ ስለሆነ ነው። የተጎዳውም የላይኛው የአንገቱ ክፍል እንጂ እግሩ ላይ አልነበረም። በእንቅስቃሴ ላይም ነበር የቆየው፤ ይህን በማየት ነው ሁለተኛውን የጨዋታ አጋማሽ እንዲጫወት ያደረግነው።”

ስለ አአ ከተማ የፍፁም ቅጣት ምት ይሰጠን ጥያቄ

“ለክስተቱ በቅርበት ያለው ዳኛው ነው። የዳኛው ውሳኔ መከበር ስላለበት ዳኛው ላይ ምንም አይነት ቅሬታ ማቅረብ አልፈልግም።”

ስለ ቡድኑ ውጤት መሻሻል

“የጀመርነውን ነገር ማስቀጠል እንፈልጋለን፤ የሚጠበቅብንም ይህ ነው። ከፊታችን ያሉ ጨዋታዎች ላይ አተኩረን መስራት ከቀጠልን የተሻለ ነገር እናመጣለን ብለን እናስባለን።”

ስለ አስናቀ ሞገስ

“አስናቀ ሞገስ ከታዳጊ ቡድን ያደገ እና በውሰት ሰጥተነው የነበረ ተጫዋች ነው። በዚህ ሰዓት ቡድናችንን ማጠናከር ስለነበረብን ከውሰት መልሰነው እኛ ቡድን ጋር ቀላቅለነዋል። አሁን ተጫዋቾች በተጎዱበት ሰዓት በመሰለፍ ጥሩ ነገር እያሳየን ነው። ይህ ልጅ እኔ በግሌም የማደንቀው ተጫዋች ነው።”

ስዩም ከበደ – አዲስ አበባ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ኢትዮጵያ ቡና በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ያሉ ልጆች ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት የሚችሉ ናቸው። አልፎ አልፎ በመስመር በኩል የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ጥሩ ነው። እንደዚያም ሆኖ ከፍተኛ ጫና አድርገዋል ማለቴ አይደለም። መሀል ሜዳ ላይ ከወትሮው በተለየ ደከም ብለን ተበልጠን ነበር።

“ኢትዮጵያ ቡናዎች የተወሰኑ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም ያን ያህል በጣም ጫና ፈጥረውብናል ብዬ አላስብም።

“እኛ ያገኘናቸው አጋጣሚዎች በጣም የሚያስቆጩ ነበሩ፤ በተለይ ኤፍሬም ቀሬ ያገኘው ኳስ…። ግን አንዳንዴ ላይሳካ ይችላል። ወደግብ ያደረግነው ሙከራም ከሌላው ጊዜ በቁጥር አነስ ይላል። በተረፈ ልጆቼ በዛሬው ዕለት ባደረጉት እንቅስቃሴ አልተከፋሁም።”

ስለ ዮናታን ብርሃኔ ጉዳት

“የዮናታን ብርሃኔ በጉዳት ተቀይሮ መውጣት ተፅዕኖ አድርጎብናል። ዮናታን በተለይ በዚህ በአበበ በቂላ ስታዲየም ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ጥሩ ይጫወታል። ባልጠበቅነው ሰዓት ነው የወጣብን።”

ስለ ዳኝነቱ

“ከሁሉ የሚያሳዝነው የዳኝነቱ ነገር ነው። እዚህ ያለው ተመልካች ለሃቅ የሚፈርድ ከሆነ ፍፁም ቅጣት ምት ለኛ መሰጠት እንደነበረበት ይናገራል። ፍፁም ቅጣት ምቱን አግኝተን ብናስቆጥር ኖሮ የተጫዋቾቻችንን ሞራል የሚገነባ ነበር። ባለፈው ሳምንት ወላይታ ድቻን ካሸነፍን በኋላ የነበረው መነሳሳት ትልቅ ነበር። እዚህም ጥሩ አጀማመር ማድረግ ችለን ነበር። የዳኝነቱ ሁኔታ ወደፊት ቢስተካከል መልካም ነው።”

ቡድኑ ውጤት በማጣቱ ምክንያት ስለሚፈጠረው ጫና

“ቡድንህ በከፍተኛ ደረጃ ተበልጦ እና ኳስ መጫወት አቅቶት ውጤት ቢያጣ ጫና ውስጥ ልትገባ ትችላለህ። እኛ ጋር ግን ይህ በተቃራኒው ነው፤ ሁልጊዜ ጥሩ እንጫወታለን። የክለቡ አመራርም ቢሆን ይህን በመረዳት ነው ቀጣዩን በተስፋ እየጠበቀ ያለው።”

Leave a Reply