​መከላከያ 2-2 ፋሲል ከተማ | የአሰልጣኞች አስተያየት

በመከላከያ እና በፋሲል ከተማ መካከል የተደረገው የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል፡፡ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞችም ጨዋታውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። 

ሻለቃ በለጠ ገብረኪዳን – መከላከያ

ስለ ጨዋታው 

” ጨዋታው እንዳያችሁት በጣም ደስ ይላል። በጣም አዝናኝ ነበር። በቡድኔ እንቅስቃሴም ብዙም አልተከፋውም ፤ ምክንያቱም በጎዶሎ ተጫውተን ነው ፈትነናቸው የወጣነው። ይኛ ቡድን ሁሌም እንደምታዩት በጎዶሎ ሆኖም 90 ደቂቃውን በተለይም ሁለተኛውን አጋማሽ በሚገባ የመጫወት ብቃቱ በጣም ጥሩ ስለሆነ በቡድኔ እንቅስቃሴ በጣም ደስተኛ ነኝ። በተጨዋቾቼም ብቃት ኮርቻለው ” 

ስለ ዳኝነቱ

” በዳኝነቱ ዙሪያ አስተያየት መስጠት አልፈልግም። ምክንያቱም እኔ ብዙ ጊዜ እዚህም ሆነ ክፍለሀገር ዳኛን ማሸነፍ ይቻላል የሚል እምነት ነው ያለኝ ። ዳኛ ሰው ነው ፤ ሊሳሳት ይችላል ፣ ዳኛ ሰው ነው ሆን ብሎም ይምጣ 90 ደቂቃ በጣም ብዙ ነው። 90 ደቂቃ ብዙ እስከሆነ ድረስም ተጨዋቾቼም  ብዙ ጊዜያቸውን ዳኛ ላይ እንዳያሳልፉ ብዙ ስራ እየሰራን ነው። ምክንያቱም ዳኛ በተቃወምክ እና ዳኛን ብዙ በተናገርክ ቁጥር የሜዳ ላይ አቋም ላይ ተፅህኖ ያደርጋል። ስለዚህ የዳኛው ውሳኔ ልክ ነበር ልክ አልነበረም ሚለውን ባለሙያ ወይም የጨዋታው ኮሚሽነር ይገምግመው። ” 

ቡድኑ በ58ኛው ደቂቃ ስላስመዘገበው ክስ 

” በሊጉ 16 ቡድኖች አሉ ። ነገር ግን 16 ዳኞች ብቻ አይደለም ያሉት። ስለዚህ ካለው የዳኞች ብዛት አንፃር አንድ ዳኛ ተደጋግሞ ማጫወት የለበትም። እሱ ላይ ቅር ብሎኛል። ዛሬ አጫውቶ ከሁለት ቀን በኋላ የሚያጫውትበት ምክንያት ትንሽ ግራ ስለገባኝ እሱ ላይ ክስ ልናስይዝ ችለናል። የፌዴሬሽኑ ዳኛ አመዳደብ ላይ ነው ቅሬታዬም። ዳኛው ከአርባምንጭ አጫውቶናል። ከሁለት ጨዋታ በኋላ ነው ድጋሚ ያጫወተን። እግር ኳስ ማደግ ካለበት ዳኞች ላይ አስትያይት እየሰጠን እና በነሱ ተፅህኖ ውስጥ እየወደቅን መሆን የለበትም። ሌሎቹም ቡድኖች ዳኛን ማሸነፍ እንደሚቻል ትምህርት ሊወስዱ ይገባል።” 

ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ፋሲል ከተማ

ስለጨዋታው 

” በኔ ስሜት ከተቃራኒ ቡድን ሰው ባይጎል መልካም ነበር። ጨዋታው ጥሩ ነበር የነበረው። እንግዲህ አንድ ተጨዋች አጭበርብሮ ከወደቀ ቢጫ ያያል። ቢጫ ካለው ደሞ ይወጣል።  እኔ ዛሬ ጥርሴን ያለማደንዘዣ የተነቀልኩኝ ያህል ነው የተሰማኝ በዳኝነቱ ምክንያት። ምክንያቱም ኤርሚያስ በትክክል ተጠልፎ ነበር። ፍፁም ቅጣት ምት ከካርድ ጋር ይገባን ነበር። በዳኝነቱ ምናልባትም ጩኸቴን የቀሙኝ ያክል ነው የተሰማኝ። ዳኝነቱ መልካም አልነበረም ። ”
ስለ ግብ ጠባቂው ብቃት 

” ምንተስኖት አቅም አለው። ግን ከታችኛው ሊግ ስለመጣ ልምድ ይፈልጋል። ይህንን በቀጣይ ጨዋታዎች ያስተካክላል። አብዛኛው የቡድኑ ተጨዋቾች ከከፍተኛ ሊግ የመጡ ናቸው። ስለዚህ ገብተው ካልሆነ ይህንን ልምድ አያገኙትም። እናም በግብ ጠባቂው ላይ ቅሬታ የለኝም። ማድረግ የሚችለውን ያክል ሰርቷል። በዋናነት ግን ቋሚ እና ልምድ ያለው ግብ ጠባቂ ያስፈልገናል። እሱ ደሞ ጉዳት ላይ ነው። ምናልባት እሱ በቀጣይ የማይደርስ ከሆነ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ እዛ ቦታ ላይ ማስተካከያ ልንወስድ እንችላለን ” 

ውጤት ስላለማስጠበቅ

” ሁልጊዜ ተጭነን ነው ምንጫወተው ። ጎዶሎም ስለነበሩ ሶስተኛ ጎል ነበር ጨዋታውን ሊገል የሚችለው። ሶስተኛውን ጎል ለማግኘት ስንጣደፍ ፊት ላይ የሰራነው ስህተት ጎል እንዲቆጠርብን አድርጓል ። የፈለገው ቢሆን ግን በልጆቼ ደስተኛ ነኝ። ጨዋታዎች ሊያልቁ ሲሉ ያሉትን ውጤቶች አስጠብቆ መውጣት አለብን። የመስመር ተከላካዮቹ ወደፊት ተጭነው ነው የሚጫወቱት። እንደዚህ እይነት አጋጣሚ ላይ ግን የምንፈልገውን ነገር አግኝተን ስለነበር ኋላቸውን ዘግተው ቢጫወቱ መልካም ነበር። ነገር ግን ይህ ጨዋታ ያስተምረናል። “

Leave a Reply