የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በስሩ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ 1ኛ ዙር በዚህ ሳምንት መጀመርያ መጠናቀቁን ተከትሎ በዳኝነት ፣ በዲስፕሊን ፣ ፀጥታ እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ግምገማ አካሂዶ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ አንኳር አንኳሮቹ የሚከተሉት ናቸው ፡-
ፕሪሚየር ሊግ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከ ሰኔ 30 ይጠናቀቃል ሲል ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ በሁለተኛው ዙር በርካታ አለም አቀፍ የክለብ እና የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ባለመኖራቸው ውድድሩ በጊዜ ሊጠናቀቅ ይችላል ተብሎ ታምኖበታል፡፡፡፡
ፀጥታ
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጨዋታዎች ላይ የሚታየውን የተመልካች ስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት እና የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ እየጣረ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ለዚህም እንዲረዳው በፖሊስ ኮሚሽን ከሚመደቡ ፀጥታ አስከባሪዎች በተጨማሪ ክለቦች የሰለጠኑ የፀጥታ አስከባሪዎችን በሜዳቸው የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ እንዲጠቀሙ ከክለቦች ጋር በትብብር ለመስራት መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡
ፌዴሬሽኑ በሪፖርቱ ላይ ለፀጥታ ችግሮች መንስኤ የሆኑት ተጫዋቾች እና በጨዋታ እለት ቡድናቸው ግጥሚያ ሳይኖረው ወደ ሜዳ የሚገቡና የሚጫወተው ቡድን ደጋፊዎችና ተጫዋቾችን የሚሰድቡ ተመልካቾች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
የዲሲፕሊን ሪኮርዶች
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛው ዙር የተመዘገቡ የቢጫ እና የቀይ ካርዶች ብዛት ይፋ ሆኗል፡፡ በ91 ጨዋታዎች በአጠቃላይ 339 ቢጫ ካርዶች ሲመዘዙ 16 ቀይ ካርዶች ተመዘዋል፡፡ ከፍተኛ ቢጫ ካርዶች ያስመዘገበው ክለብ አርባምንጭ ከነማ ሲሆን ከፍተኛውን ቀይ ያስመዘገበው ክለብ ኢትዮጵያ መድን ነው፡፡ በተጫዋች ደረጃ ደግሞ 2 ቀይ ካርዶች የተመለከተው የመብራት ኃይሉ በረከት ይስሃቅ ይመራል፡፡
ዳኞች
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚታየው የዳኝነት አመዳደብ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ፋና-ስፖርት ዘግቧል፡፡ ዳኞችን የመመደብ ኃላፊነት ያለው በግለሰቦች ደረጃ በመሆኑም ለሃሜት ክፍት እንዲሆን እንዳደረገው ይነገራል፡፡ እንደ ዘገባው ዳኞች ከኮሚሽነሮች ጋር ያላቸው ግንኙነት ከሻከረ ጨዋታዎችን በጥሩ ሁኔታ ቢመሩ እንኳን የተዛባ ሪፖርት እንደሚቀርብባቸው ቅሬታ ያሰማሉ፡፡
በሁለተኛው ዙር . . .
በሪፖርቱ በሁለተኛው ዙር ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ከክለብ ተወካዮች ሃሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ ከነዚህምመካከል ፡-
-የዝውውር ደንቡ እንዲሻሻልና በዝውውር ሂደቱ የማያስፈልጉ ሰንሰለቶች እንዲበጠሱ ጥቆማ ቀርቧል፡፡ በአመቱ መጀመርያ ተሻሽሎ የረቀቀው የዝውውር ደንብ እስካሁን ለምን እንዳልፀደቀም ከተወካዮች ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ፌዴሬሽኑ አዲሱን ደንብ ያላፀደቀበት ምክንያት በሽግግር ላይ በመሆኑ እንደሆኑ ተገልጧል፡፡
-በውድድር ዘመኑ መገባደጃ አካባቢ የሚታዩትን ሆን ተብሎ የጨዋታ ውጤትን የማስቀየር ችግሮች እንዲቀረፉ ተጠይቋል፡፡ በተለይም በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚጫወቱ ክለቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ጨዋታ ሲያደርጉ በጥንቃቄ እንዲታዩ ጥቆማ ቀርቧል፡፡
{jcomments on}