የወላይታዋ ቦዲቲ የ2ኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመርያ ግጥሚያን ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ የመጀመርያው 5 ውስጥ ያሉት ሁለቱ ክለቦች በውድድር ዘመኑ መክፈቻ ያደረጉትን ጨዋታ የሚያስታውሰንን ፍልሚያነገ በ9፡00 ቦዲቲ ላይ ያደርጋሉ፡፡
ነገ ሁለቱም በመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎቻቸው የደረሰባቸውን ሽንፈት በመቀልበስ ለማገገም አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወላይታ ድቻ ባለፈው ሰኞ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ የሊግ ሽንፈት አስመዝግቧል፡፡ በመከላከሉ ጠንካራ እንደሆነ የተነገረለት ቡድንም በሰማያዊዎቹ በውድድር ዘመኑ በአጠቃላይ የተቆጠረበትን ግብ የሚልቅ ግብ ተቆጥሮበታል፡፡ በ23 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ንግድ ባንክ በበኩሉ ከ20 ቀናት በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 የተሸነፈበት ጨዋታ የመጨረሻ ጨዋታ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡
የነገውን ጨዋታ አጓጊ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ በመከላከሉ ጠንካራ የሆኑትና ግብ ለማስቆጠር የሚቸገሩት ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው ምን አይነት አቀራረብ እንደሚኖራቸው ማየት ነው፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በ3-5-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ሲጠበቅ አሰልጣኝ ፀጋዬ በቀኝ መስመር ላይ ያሉት ተጫዋቾቹ በመጎዳታቸው ምናልባትም በተለየ አሰላለፍ ሊገባ ይችላል፡፡
ንግድ ባንክ ወሳኝ አጥቂው ፊሊፕ ዳውዚ በውድድር ዘመኑ በተመለከታቸው 5 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ምክንያት አብደላ ሸምሱ እና ተክሉ ተስፋዬ ደግሞ በጉዳት የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል፡፡
‹‹ በነገው ጨዋታ የ1ኛው ዙር ውጤት ይደገማል ብላችሁ እንዳትጠብቁ፡፡ ለጨዋታው በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡ ቡድኔ ከጨዋታ ጨዋታ እየተዋሃደና መሻሻሎችን እያሳየነው፡፡ ›› ያሉት የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ናቸው፡፡
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው ‹‹ ለተጋጣሚያችን ክብር አለን፡፡ ለጨዋታውም ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ካለፈው ሽንፈታችን በፍጥነት ለማገገም እየሰራን ነው ›› ብለዋል፡፡
እውነታዎች
-ወላይታ ድቻ ቦዲቲ ላይ የሚያደርገው 4ኛ ጨዋታው ነው፡፡ ድቻዎች በቦዲቲ ስታዲየም 3 ጨዋታዎችን አድርገው መከላከያን ሲረቱ ከዳሽንቢራ እና ሀዋሳ ከነማ ጋር አቻ ተለያይተዋል፡፡
-ንግድ ባንኮች ከአዲስ አበባ ውጪ 4 ጊዜ ተጫውተው 2 ሲያሸንፉ 2 አቻ ወጥተዋል፡፡
-ሁለቱ ቡድኖች በውድድር ዘመኑ መጀመርያ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ንግድ ባንክን በሳምሶን ኮሌቻ ፣ ባዬ ገዛኸኝ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና ዮሴፍ ዴንጌቶ ግቦች 4-0 አሸንፏል፡፡
የወንድማማቾች ፍልሚያ
ሁለቱም ድንቅ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ነው፡፡ ታላቅየው መሃሪ መና በውድድር ዘመኑ ለንግድ ባንክ 2 ግቦች ሲያስቆጥር በሴካፋም ኢትዮጵያን ወክሏል፡፡ ታናሽየው እሸቱ መና ደግሞ በድቻ የቀኝ መስመር ላይ ቁልፍ ሚና እየተወጣ የሚገኝ ከፊቱ ብሩህ ጊዜያት የሚጠብቁት ወጣት ነው፡፡
ሁለቱ በአንድ መስመር ላይ መጫወታቸውና በሁለቱም አሰልጣኞች ሲስተም ውስጥ ቁልፍ ሚናን የሚተገብሩ መሆናቸው ትኩረትን ይስባል፡፡ ሁለቱም የመስመር ተከላከዮች ቢሆኑም ቡድኖቹ በ3-5-2 አሰላለፍ የሚገቡ ከሆነ እሸቱ በቀኝ መስመር ፣ መሃሪ ደግሞ በግራ መስመር በቀጥታ ለመፋለም ይገደዳሉ፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነቶች
ተጫወቱ – 1
ድቻ አሸነፈ – 1 (4 ግብ)
አቻ – 0
ንግድ ባንክ አሸነፈ – 0 (0 ግብ)
{jcomments on}