የጨዋታ ​ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ ካለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደተጀመረ ድሬዳዋ ከተማ በሀብታሙ ወልዴ አማካይነት ሙከራ ማድረግ ቢችልም ተጨማሪ ሙከራ ለማድረግ ረጅም ደቂቃዎች ወስዶበታል፡፡ ይልቁንም ሀዋሳ ከተማዎች እጅግ ያለቀላቸው ኳሶችን ሲያመክኑ የእንቅስቃሴ የበላይነትም አሳይተዋል፡፡

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው የመስመር አማካዩ ፍሬው ሰለሞን በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተደጋጋሚ ለግብ የቀረቡ ሙከራወችን ሲያደር ተስተውሏል፡፡ በተለይ በ3ኛው ፣ 6ኛው እና 23ኛው ደቂቃዎች ላይ እጅግ ለማመን የሚከብዱ ኳሶችን ሲያመክን ተስውሏል፡፡ በተለይ በ14ኛው ደቂቃ ፍርዳወቅ ሲሳይ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ታካ ለጥቂት የወጣችው ኳስ ሀዋሳን መሪ ልታደርግ የምችል ነበረች፡፡

ሀዋሳ ከተማወች በመጀመሪያው አጋማሽ ፍሬው ሰለሞን ካመከናቸው ኳሶች በተጨማሪ በ18ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደርቤ ያሻገረውን ኳስ ፍርዳወቅ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በተመሳሳይ ቦታ ሁለት ጊዜ ከ25 ሜትር ርቀት ጋዲሳ መብራቴ አክርሮ መትቶ ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው ሳምሶን አሰፋ በአስደናቂ ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡

በድሬዳዋ በኩል በ1ኛው ደቂቃ ከተሞከረው ሙከራ ውጪ በ20ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ወልዴ ብቻውን እየገፋ ሲገባ ሜንሳህ ከእግሩ ላይ የወሰደበት ኳስ ብቻ ተጠቃሽ ነበር፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብዙ ውዝግቦች የተከሰቱ ሲሆን በዚህኛው አጋማሽም የሀዋሳ የበላይነት ቀጥሏል፡፡ በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማዎች የአቻ ውጤት ይዞ ለመውጣት በሚመስል መልኩ የመከላከል ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾችናን ቀይረው በማስገባት ያሰቡትን ማሳካት ችለዋል፡፡

በ53ኛው ደቂቃ የጨዋታውን መልክ የቀየረ ተግባር ተከስቷል፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጨዋታው ያለቀላቸውን ኳሶች ሲያመክን የነበረው ፍሬው ሰለሞንን ከረጅም ጊዜ ጉዳት የተመለሰው ዮናታን ከበደን ቀይረው ባስገቡበት ውሳኔ ፍሬው ውበቱ አባተ ላይ ያልተገባ ባህሪ በማሳየት ከአጥሩ ውጭ ለመውጣት ሲሞክር ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች መልሰውታል፡፡ ደጋፊውም ፍሬው በመውጣቱ አሰልጣኝ ውበቱ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ሀዋሳዎች 3 ነጥብ ለማግኘት ይበልጥ ተጭነው በርካታ የግብ እድሎች መፍጠር ቢችሉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በ67ኛው ደቂቃ ዩናታን ከበደ በግንሩ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ኤፍሬም ያመከነው ፤ ፍርዳወቅ ሲሳይ ከግብ ጠባቂው ሳምሶን ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ ተጠቃሽ  ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ድሬዳዋ ከተማዎች እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በጥብቅ መከላከል 1 ነጥብ አሳክተው መውጣት ሲችሉ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል የደረሱባቸው አጋጣሚዎች እጅግ ጥቂት ነበሩ፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ሲረጋ ሀዋሳ ከተማ ያገኘውን አንድ ነጥብ ተጠቅሞ የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ ለአዲስ አበባ ከተማ አስረክቧል፡፡

አስተያየቶች

ዘላለም ሽፈራው – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ እነሱ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ቢሆንም ለእኛ ውጤቱ ባያስከፋም ብናሸንፍ ደስ ይለን ነበር፡፡ ሀዋሳ ያለበት ደረጃ ጥሩ ስላልነበር ያን ሰለማውቅ ተከላካይ አብዝቼ ተጠቅሜያለሁ፡፡  ባናሸንፍም ከሜዳ ውጭ አንድ ነጥብ መያዛችን አያስከፋም፡፡

በቀጣይ. . .

ክለቡን ለማጠናከር ሶስት ተከላካይ ከጋና አስፈርመናል ይህም በሁለተኛው ዙር ተሻሽለን እኖድንቀርብ ያደርገናል፡፡

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታውን ተቆጣጥረን እንደመጫወታችን ማሸነፍ እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን በቀላሉ እያመከንን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ ይህ ተደጋጋሚ ዋጋ አሰከፍሎናል፡፡ ”

ስለ ፍሬው 

“ፍሬው ያሳየው ባህሪ አይገርመኝም፡፡ ደጋፊወቹ ያነሱት ተቃውሞ ፍሬውን ደግፈው ሊሆን ይችላል፡፡ በውጤቱም መከፋታቸውንም እረዳለሁ፡፡ ” 

Leave a Reply