የጨዋታ ሪፖርት | የመሪዎቹ ፍልሚያ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

​በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ደደቢት እና አዳማ ከተማ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል ። 

እስከ 12ኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ሊጉን በአንደኛ እና በሁለተኛነት ይመሩ የነበሩት የአዳማ ከተማ እና የደደቢት መገናኘት ጨዋታውን ከፍተኛ ግምት እንዲሰጠው ያደረገ ነበር። ከሁለቱ ጨዋታ በፊትም ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመርታት የሊጉን መሪነት በመረከቡ የዚህ ጨዋታ ውጤት በሊጉ መሪነት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ለጨዋታው ቀድሞውንም የተሰጠውን ግምት ይበልጥ ከፍ እንዲል አስገድዷል ።
ከመጀመሪያው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ስታድየሙን ያለቀቁትን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ጨምሮ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች በስታድየሙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በመገኘት ጨዋታው ጥሩ ድባብ እንዲላበስ አድርገውት ነበር። ነገር ግን የጨዋታው አጠቃላይ ሂደት በተለይም የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ ተጠባቂነቱንም ሆነ የደጋፊውን ድባብ በብዙ መስፈርቶች ያልመጠነ ሆኖ ታይቷል ።

በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በ13ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ  በግራ መስመር ከአዳማዎች ሳጥን ውስጥ የሞከረው ኳስ ወደውጪ ከወጣ በኋላ ሌላ ሙከራ ለመመልከት እስከ 30ኛው ደቂቃ መጠበቅ የግድ ነበር ። በ30ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያሻማለትን ኳስ የግራ መስመር አማካዩ ኤፍሬም አሻሞ በግንባሩ ሞክሮ ወደውጪ ወጥቶበታል ። ከዚህ የመጀመሪያው ግማሽ ብቸኛ አደገኛ ሙከራ ሌላ ጌታነህ ከበደ 43ኛው ደቂቃ ላይ በቅርብ ርቀት አግኝቶ ያማከነው ኳስ ይጠቀስ እንደሆን እንጂ ሌላ ሊጠቀስ የሚችል ሙከራ አልተመለከትንም።

ከዚህ ውጪ የመጀመሪያው አጋማሽ መሀል ሜዳ ላይ በተወሰኑ ተደጋጋሚ እንቅስቃሴዎች የሚቆራረጡ አጫጭር እንዲሁም ያልተመጠኑ ረጃጅም ኳሶችን እና እነሱን ተከትለው ይታዩ በነበሩ የእጅ ውርወራዎች የታጀበ ነበር ። የተጨዋቾች ግጭት እና ጉዳቶችም እንዲሁ ጨዋታውን በተደጋጋሚ ሲያቋርጡት ተስተውሏል።

ሁለተኛውም ግማሽ በተመሳሳይ መንፈስ ጀምሮ በ52ተኛው ደቂቃ ላይ ከአልቢተሩ ጋር በመከራከር የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተው አጥቂው ሚካኤል ጆርጅ በ55ተኛው ደቂቃ ላይ የደደቢት ተከላካዮች አለመግባባት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ተጠቅሞ በጨዋታው ለአዳማዎች የመጀመሪያ የግብ ሙከራ አድርጓል ። ጨዋታው የተሻለ መነቃቃት ታይቶበትም ጌታነህ ከበደ ከ እንድ ደቂቃ በኋላ ከመሀል በተላከለት ኳስ ግብ ጠባቂውን ጃኮብ ፔንዚን አልፎ ቢሞክርም የግቡ ቋሚ መልሶበታል።

59ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም የአሻሞን መላያ በመጎተት ሲሳይ ቶሊ ከአዳማዎች በኩል በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣ ሲሆን ይህን ተከትሎም አዳማዎች ጥላሁን ወልዴን በግራ መስመር ተከላካይነት በመተካት ሚካኤል ጆርጅን ቀይረው ከሜዳ አስወጥተዋል ። ከዚህ በኃላ የነበረውን የጨዋታ ክፍለጊዜም አዳማዎች መከላከል ላይ አመዝነው አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት የተጋጣሚያቸውን ጎል ለመፈተሽ ሲሞክሩ ታይተዋል ። ከዚህም አጨዋወት በመነሳት በ83ኛው ደቂቃ ፋሲካ አስፋው ከሳጥን ውጪ ጥሩ ኳስ ሞክሮ በግቡ አናት ወጥቶበታል ።

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች በበኩላቸው በአጫጭር ኳሶች የአዳማ ከተማዎችን የመከላከል መስመር ማለፍ አላዋጣ ስላላቸው ይመስላል ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂዎች ለማድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል ። በዚህም አጨዋወት ቢሆን ደደቢቶች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ቢታይም ከተጋጣሚያቸው አንፃር ግን የተሻለ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል ። በ63ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከኤፍሬም አሻሞ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ጃኮብ ፔንዚ ያዳነበትን እና በ73ተኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን ከአዳሞዎች ሳጥን ጠርዝ ላይ ጥሩ ዕድል አግኝቶ ሲሞክር በጎን የወጣበትን አጋጣሚዎችንም ለዚህ እንደማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል ።

ጨዋታው ወደ መገባደጃው ሲቃረብም አልቢትሩ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በተደጋጋሚ ከተጨዋቾች ጋር ውዝግብ ውስጥ ሲከቷቸው እና አላስፈላጊ ግርግርሮች ሲፈጠሩ በተደጋጋሚ እየተጎዱ ይወድቁ ከነበሩ ተጨዋቾች ሁኔታ ጋር ተደምሮ ጨዋታው አዝናኝነቱ እጅግ እንዲወርድ አድርጎታል፡፡

በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎችም በተደጋጋሚ የቢጫ ካርዶች ከመመዘዛቸው ውጪ በ89ኛው ደቂቃ ስዩም ተስፋዬ ያሾለከለትን ኳስ ጌታነህ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ሞክሮ በተከላካዮች ሲመለስበት በጭማሪ ደቂቃ ላይም የግብ ጠባቂውን ጃኮ ፔንዚ ስህተት ተከትሎ አክሊሉ አያነው ጥሩ እድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቶቷል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላም ዳኛቹ በደደቢት ተጨዋቾች ተከበው የተዋከቡ ሲሆን ብርሀኑ ቦጋለም የቢጫ ካርድ ሊመለከት ችሏል። የአዳማ ከተማ ተጨዋቾችም ለድብድብ እየተጋበዙ ነበር ወደመልበሻ ክፍል የገቡት። ይህ በተጨዋቾቹ መሀል የነበረው ጥሩ ያልሆነ መንፈስ ወደ ደጋፊዎችም አምርቶ በካታንጋ በኩል ከውጪ በሚወረወር ድንጋይ ምክንያት በሽሽት የሚሯሯጡ ደጋፊዎች የታዩ ቢሆንም ሁኔታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ተመልካቹ ከስታድየሙ ወጥቷል ።

ይህ ለተመልካች አዝናኝ ያልነበረ ጨዋታም ያለግብ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመሪነቱ ቀጥሎ ሁለቱ ተጋጣሚዎች አዳማ ከተማ እና ደደቢትም በ25 እና እና በ24 ነጥቦች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል ።

Leave a Reply