​የጨዋታ ሪፖርት | ወልድያ ወደ ጅማ ተጉዞ ታሪካዊ ድል አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ሲደረጉ ወደ ጅማ ተጉዞ ጅማ አባ ቡናን የገጠመው ወልድያ 2-0 በማሸነፍ በክለቡ ታሪክ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል አስመዝግቧል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ ጅማ አባ ቡና የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበረው ቢሆንም ብልጫውን ወደ ግብ እድሎች መቀየር አልቻለም፡፡ ዩጋንዳዊው አማካይ ክርስቶፈር ንታንቢ ከርቀት የሞከራቸው አደገኛ ኳሶች በጅማ አባ ቡና በኩል ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

በዚሁ የመጀመርያ አጋማሽ ወልድያ በጥብቅ በመከላከል እነና በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ የጅማ አባ ቡናን የተከላካይ መስመር የፈተሹ ሲሆን የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ አንዱአለም ንጉሴ በግል ጥረቱ የአባ ቡናን የተከላካይ መስመር ሲፈትን ውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ወልድያ ተሻሽሎ የቀረበ ሲሆን በጫላ ድሪባ እና አንዱአለም ንጉሴ አማካኝነት ጫና በመፍጠር 3 ነጥቦች ይዞ የወጣባቸውን ግቦች ማስቆጠርም ችሏል፡፡

በ65ኛው ደቂቃ አንጋፋው አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ የጅማ አባ ቡና ተከላካይ መስመር ክፍተትን በመጠቀም የወልድያን ቀዳሚ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ ደግሞ አንዱአለም ከመስመር ያሻገረውነ ኳስ ታደለ ምህረቴ ለማውጣት ሲሞክር በራሱ ላይ አስቆጥሮ የወልድያን መሪነት ወደ 2 አስፍቷል፡፡

በርካታ ካርዶቸች በተመዘዙበት 2ኛው አጋማሽ በወልድያ በኩል 6 ቢጫ ካርድ ሲመዘዝ 2 ቢጫ ካርድ በጅማ አባ ቡና በኩል ተመዝግቧል፡፡ የወልድያው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ደግሞ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተ ተጫዋች ነው፡፡

በውጤቱ የተበሳጩ የጅማ አባ ቡና ደጋፊዎች በቡድኑ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ በተለይ ሁለተኛው ግብ ከተቆጠረ በኋላ በርካታ ደጋፊዎች ስታድየሙን ለቀው ወጥተዋል፡፡

ድሉን ተከትሎ ወልድያ በፕሪምየር ሊግ ታሪኩ የመጀመርያውን የሜዳ ውጪ ድል ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በደረጃ ሰንጠረዡ ወልድያ በ17 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ከደረጄ በላይ ጋር ተለያይቶ ገብረመድህን ኃይሌን አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው ጅማ አባ ቡና በነበረበት 14ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል፡፡

Leave a Reply