​ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ | የአሰልጣኞች አስተያየት

በፕሪምየር ሊጉ 13ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአዳነ ግርማ የሁለተኛ አጋማሽ ግብ ተሸንፏል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

ስለጨዋታው

“ማሸነፍ ነበር የምንፈልገው ፤ በጥሩ ሁኔታ አሸንፈን ወጥተናል፡፡ የዛሬው ጨዋታ ከሌላው ጊዜ የሚለይበት ብዙ ነገሮች የሉም፡፡ ከሽንፈት እና ከጥሩ አለመጫወት ስለመጣን የቡድናችን አቋም ጥሩ አልነበረም፡፡ ውጤቱ ለተጫዋቾችቻችን እና ደጋፊዎቻችን ጥሩ ነገር ነው ብዬ አስባለው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ እኛ አጥቅተን ተጫውተናል፡፡ ብዙ የግብ እድሎችን ባናገኝም ተጫውተናል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ስርዓታችንን ቀይረን ተጫውተን በእነሱም በእኛም በኩል የማጥቃት አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ያገኘነውን አጋጣሚ ተጠቅመን ውጤቱን ይዘን ወጥተናል፡፡”

የሊግ ፉክክር

“ይሄ ቡድን የምትለው የለም፡፡ ሁሉም ቡድን ጠንካራ ነው፡፡ ሁሉም ቡድን የሚጫወተው ለማሸነፍ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የእትዮጵያን እግርኳስን ልናሳድግበት የምንችላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ግን ቀጣይነት ካለው ነው፡፡ ሁሉም ቡድን ለዋንጫ የሚጫወት ከሆነ ጥሩ ነገር የምናይ ይሆናል፡፡”


የኢትዮ-አሌክትሪክ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው በመጀመሪያው 45 ላይ የተሻለ ነበር፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ሚዛናዊ እንቅስቃሴ ነበር ያደረጉት፡፡ የገባብን ኳስ በግብ ጠባቂው እና በተከላካይ ስህተት ነው፡፡ ከዛ በኃላ እንዳያችሁት ሙሉ ለሙሉ አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል፡፡ ከሶስት ከአራት በላይ የሚሆኑ በርካታ የግብ እድሎችን ፈጥረናል፡፡ ጨዋታውን ተቆጣጥረናል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ጊዮርጊስ ቆሞ አሸንፎ ወጥቷል ማለት ይቻላል፡፡”

ስለዳኝነት ውሳኔ (የተስፋዬ መላኩ እና አብዱልከሪም ኒኪማ ቀይ ካርድ)

“የዳኛው ውሳኔ ትክክል ነው፡፡ ተጫዋች አንዳንድ ጊዜ ስሜታዊ ይሆናል፡፡ የጨዋታው ውጤትም አለ ፤ ከዛ ጋር በተያያዘ ለግጭት ቅርብ ናቸው፡፡ ስሜታዊ ስለሚሆኑ አንዳንድ ግዜ እንደዚህ ዓይነት ነገር ይፈጠራል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *