​ደደቢት 0-0 አዳማ ከተማ | የአሰልጣኞች አስተያየት

የሊጉ አናት ላይ የነበሩትን ሁለቱን ክለቦች ባገናኘው የፕሪምየር ሊጉ 13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ደደቢት እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ መሪነቱን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያስረክብ ደደቢት ወደ ሶስተኛነት ተንሸራቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የደደቢት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ

ስለጨዋታው 

“የዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነው ፤ ግን የምንፈልገውን ውጤት አላገኘንም፡፡ እንግዲህ ኳስ ላይ እንደዚህ ያጋጥማል፡፡ ሶስት ነጥብ ነበር የፈለግነው አልሆነም አንድ ነጥብ ይዘን ወጥተናል፡፡ ከእረፍት በኃላ ብዙ ወደ ግብ ሞክረን ነበር አልተሳካም፡፡ ገና ብዙ ጨዋታ ስላለ እናስተካክላለን ማለት ነው፡፡ የዛሬው ጨዋታ ውጤቴ እንደጠበኩት አይደለም፡፡”

የተጫዋች ቁጥር ብልጫን አለመጠቀም

“የቁጥር ብልጫን አግኝተን ነበር፡፡ ግን እንዳገኘን ወደ ግብ ብዙ ቀርበናል፡፡ ብዙ ግቦችን ስተናል፡፡ ተከላካዮችም ግብ ጠባቂውም ኳስን አውጥቷል፡፡ አዳማዎች የፈለጉት ይህንን ነበር፡፡ በመልሶ ማጥቃት ነበር ይጫወቱ የነበሩት፡፡ ስለዚህ ብዙ ግዜ ወደ እኛ ግብ ክልል ስለማይሄዱ ግብ እንዳይገባባቸው ነበር ትግል የነበረው፡፡ ትግላቸውን ፈፅመዋል፡፡ እየተኙ 45 ደቂቃውን ጨርሰዋል ማለት ይቻላል፡፡”

በጨዋታው ጉሽሚያ መብዛቱ

“ከመጀመሪያው ተመልክታችሁ እንደሆነ የኃይል ጨዋታ የጀመሩት እነሱ ናቸው፡፡ ምክንያቱ ጨዋታ ለማበላሸት ነው፡፡ የአንድን ተጫዋች እንቅስቃሴ ለማበላሸት ነው፡፡ በእጃቻውም በእግራቸውም ከመጀመሪያው ጀምሮ እነሱ ናቸው የተጫወቱበት፡፡ ግን እንደ ታክቲክ ነው የተጠቀሙበት፡፡ ረድቷቸዋልም፡፡ ይህንን ጨዋታ ባይጫወቱ ኳስ ብቻ ቢጫወቱ ኖሮ ተሸንፈው ይወጡ ነበር፡፡ የልጆቹን ስሜት እና ሞራል መስረቅ ስለሆነ ይህ ታክቲክ ስለዚህ ተጠቅመውበታል፡፡”

የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ትግል የበዛበት ነው፡፡ በሁለታችንም በኩል ጥሩ የኳስ ፍሰት አልነበረም፡፡ ስለዚህ ውጤቱን መቀበል ብቻ ነው፡፡ እንዳሰብነው አይደለም የተንቀሳቀስነው፡፡ የኃይል ጨዋታ ስላመዘነ በሁለታችንም በኩል ይህ ነው ለማለት ያስቸግራል ዞሮዞሮ መከላከሉ ላይ በተሻለ ጠንክረን ተከላክለናል፡፡ እነሱም ተከላክለዋል፡፡ የኳስ ፍሰቱ በብዛት ወደፊት አልሄደም፡፡ መሃል ሜዳ ላይም እንደምፈልገው ልንጫወት አልቻልንም፡፡ በታክቲካ ዲሲፕሊን የታጠረ ነው፡፡ አስራትም ሃገራችን ላይ ካሉ ምርጥ አሰልጣኞች አንዱ ነው፡፡ የመዝጋት አቅሙ ጥሩ ነው፡፡ ዕምብዛም የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር አልቻልንም፡፡”

የወሳኝ ተጫዋቾች ጉዳት

“ወሳኝ የምንላቸው ተጫዋቾች አሁን ታፈሰ (ተስፋዬ)፣ ሱሌማን (መሃመድ) በጣም ወሳኝ ተጫዋቾቻችን ናቸው፡፡ ቡድኑ በእነሱ ላይ ብቻ የተመሰረተ ስላልሆነ ባሉት ልጆች ቡድንን ይዞ መቅረቡ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ የሚቀጥለው ውድድር ጣፋጭ መሆን የእኛ አቻ መውጣት አስተዋፅኦ አለው፡፡ ውድድሩም ያምራል እኛም ጠንክረን እንሰራለን፡፡”

በጎዶሎ መጫወት

“ማሸነፉ የበለጠ ያስደስተን ነበር፡፡ ሲሳይ ደግሞ ሌላው የማጥቂያ መስመራችን ነበር የተጠቀምንበት፡፡ ከእሱ የሚወጡ ኳሶች ጥሩ ናቸው፡፡ የእሱ መውጣት ለዚህ ጨዋታ ብቻ አልነበረም ለቀጣይም ይጎዳናል፡፡ የእሱ መውጣት እንድናፈገፍግ አድርጎናል ምክንያቱም በ10 ልጅ ረጅም ደቂቃ መጫወት ከባድ ነው፡፡”

Leave a Reply