አዲስ አበባ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ እየተሳተፈበት በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጥፎ የሚባል የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ወላይታ ድቻን ከ8 ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ በማሸነፍ ወደ ድል ቢመለስም ረቡዕ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ 1-0 ተሸንፎ ባለበት 8 ነጥብ ለመርጋት የመጨረሻውን ደረጃ ለመያዝ ተገዷል፡፡
ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የክለቡ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድናቸውን ለማጠናከር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አአ ከተማ በሁለተኛው ዙር የተለየ መልክ ሊኖረው እንደሚችልም የአሰልጣኙ አስተያየት ጠቋሚ ነው፡፡
“በሁለተኛው ዙር ለመጠናከር በተለያየ ቦታ ላይ ክፍተቶቻችንን ሊደፍኑ የሚችሉ ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾችን ከውጪ አግኝተናል፡፡ 6 ተጫዋቾች ከካሜሩን ፣ ጋና እና ናይጄሪያ መጥተዋል። በአጥቂ እና አማካይ ክፍል ላይ ጥሩ ተጫዋቾችን እናስፈርማለን ብዬ አስባለሁ። በዚህ ተስፋ እየሰራን ነው ያለነው።” ብለዋል፡፡
ክለቡ ከዲሲፕሊን እና ተደጋጋሚ ጉዳት ጋር በተያያዘ ተጫዋቾችን ከስብስቡ በመቀነስ ክለቡን ሊያገለግሉ የሚችሉ ተጫዋቾችን ብቻ ለመጠቀም እንደተዘጋጁ አሰልጣኝ ስዩም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
“የዲሲፕሊን እርምጃ የተወሰደባቸውን ሁለት ተጫዋቾች ከቡድኑ ቀንሰናል። በጉዳት ምክንያት ይሄን ክለብ ሊጠቅሙ የማይችሉ ሁለት ተጫዋቾችም አሉ። ቡድኑ ከመውረድ መትረፍ ስላለበት እነዚህ ተጫዋቾችም ቦታውን መልቀቅ ይኖርባቸዋል። ቡድኑን እንደገና በማደስ ሂደት ውስጥ ነው ያለነው። በሁለተኛው ዙር ተጠናክረን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ።”
ሶከር ኢትዮጵያ የተቀነሱትን ተጫዋቾች ማንነት ለማወቅ ባደረገችው ማጣራት 3 ተጫዋቾች በጉዳት ፣ 2 ተጫዋቾች ደግሞ በዲሲፕሊን ጉዳይ ተቀንሰዋል፡፡
ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ የነበረውና የክለቡን የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጎል ያስቆጠረው ኃይለየሱስ መልካ እና በክረምቱ ከሱሉልታ ከተማ ቡድኑን የተቀላቀለው ኤርሚያስ ዳንኤል ክለቡ በዲሲፕሊን ምክንያት የቀነሳቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ተጫዋቾቹ በራሳቸው ውሳኔ ከክለቡ ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በጉዳት ምክንያት ለክለቡ ምንም ጨዋታ ያላደረገው አማካዩ ሱራፌል ጌታቸው እና የረጅም ጊዜ ጉዳት ያስተናገደው አልሳዲቅ አልማሂ ከስብስቡ የተቀነሱ ተጫዋቾት ናቸው፡፡ ከድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮ ቡድኑን የተቀላቀለውና በተደጋጋሚ ጉዳት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ መሰለፍ የቻለው ሲሳይ ደምሴም ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመለያየት የተቃረበ ተጫዋች ነው፡፡
በተያያዘ ዜና ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ተከትሎ ለቡድኑ አባላት ቃል የተገባላቸው የሽልማት ገንዘብ እስካሁን አለመፈፀሙ በቡድኑ አባላት ላይ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ በጉዳዩ ዙርያ ለክለቡ በተደጋጋሚ ጥያቂ ቢያቀርቡም ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውንም ከክለቡ አካባቢ ያገኘነው መረጃ ያለመክታል፡፡
© በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር ሙሉ ለሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ ፅሁፎቹን በሌላ ሚድያ ሲጠቀሙ ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡