​ዝውውር | ኢትዮጵያ ቡና ጋናዊ ተከላካይ አስፈረመ

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ጋናዊው ተከላካይ ሳምሶን ኩድጆን እንዳስፈረመ አስታውቋል። ሳምሶን የአንድ አመት ውል ከክለቡ ጋር ተፈራርሟል፡፡

የ28 ዓመቱ ተከላካይ የእግርኳስ ህይወቱን በቱንዱ ማይቲ ጄትስ ክለብ ወጣት ቡድን ውስጥ የጀመረ ሲሆን የማይቲ ጄትስ ዋናው ቡድን፣ ማዴማ ስፖርት ክለብ፣ አሻንቲ ጎልድ እና የጋናው ታላቅ ክለብ አክራ ኸርትስ ኦፍ ኦክ ተጫውቶ ያሳለፈባቸው ክለቦች ናቸው። ኩድጆ ወደ አውሮፓ በማቅናትም በፊንላንዱ ክለብ ኤፍሲ ሆንካ የ6 ወራት ቆይታ ነበረው።

ሳምሶን ኩድጆ በጋና የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተጫወተ ሲሆን በሃገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ በሚሰለፉበት የአፍሪካ እግርኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ማጣሪያዎች እና ኮትዲቯር ባዘጋጀችው የ2009ኙ ውድድር ላይ የሃገሩን ማሊያ አድርጎ ተጫውቷል፤ በ2012ም ለዋናው የጋና ብሔራዊ ቡድን መጠራት ችሎ ነበር።

በአንድ ወቅት በአልጄሪያው ክለብ ኢኤስ ሴቲፍ እና በካይሮው ትልቅ ክለብ ዛማሌክ ሲፈለግ የነበረው እና ያለፉትን 3 የውድድር ዓመታት በኸርትስ ኦፍ ኦክ ያሳለፈው ተጫዋቹ ሰፊ ልምድ ያለው መሆኑ እንዲሁም ከመሃል ተከላካይ ቦታ በተጨማሪ የተከላካይ አማካይ እና የአጥቂ አማካይ ስፍራዎች ላይ መጫወት መቻሉ አዲሱ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡናን በብዙ መንገድ መጥቀም የሚችል ተጫዋች ያደርገዋል።


© በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር ሙሉ ለሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ ፅሁፎቹን በሌላ ሚድያ ሲጠቀሙ ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

1 Comment

  1. በጣም በጣም ጐበዝ ናቸሁ በርቱ ቀጥሉበት፡፡ ግን ከጫወታ በፊት ግምታዊ አስተላለፍ ግምታዊ ውጤቶች በተለያዩ እንግዶች(ባለሙያዎች) ብታቀርቡ፡፡ቅድሜ ግምታዊ ግምት የጫዎታ ዉጤቶች Online ለአንባብዎች ብታቀርቡ፡፡ የእለቱን የጫዎታ ኮከብ ተጫዋች የወሩን ብታስመርጡን፡፡
    በተረፈ በጣም ተምችቶናል በርቱ፡፡

Leave a Reply