ወልድያ እና አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ሊለያዩ ተቃርበዋል

የወልድያው አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ከክለቡ ጋር ለመለያየት የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል፡፡ ከቡድኑ ጋር አብረው ወደ ወልድያ ያልተጓዙ ሲሆን በመጪው ማክሰኞ ኤሌክትሪክን በሚያስተናግዱበት ጨዋታ ቡድኑን ላይመሩም ይችላሉ፡፡

ወልድያን ከከፍተኛ ሊጉ በማሳደግ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የ13 ሳምንታት ጉዞ ቡድኑ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ እንዲገኝ ያደረጉት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በተለይም ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በተነሳው የደጋፊ ተቃውሞ ደስተኛ እንዳልሆኑ እና ይህም መልቀቂያ ለማስገባት እንዳነሳሳቸው ከክለቡ አካባቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ክለቡ አሰልጣኙ የሚፈልጉትን ነገሮች ማሟላት አለመቻሉ ለመልቀቂያ ጥያቄው እንደ መንስኤ ተወስዷል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ስለጉዳዩ ባደረገችው ማጣራት ክለቡ መልቀቂያ ደብዳቤ እንደደረሰው ያመነ ሲሆን በውይይት ውሳኔያቸውን ለማስቀየር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አረጋግጣለች፡፡

ወልድያ ስፖርት ክለብ የዘመናዊ ስታድየም ባለቤት ከመሆን ባሻገር በገንዘብ ችግር ፣ በተጫዋች የዲሲፕሊን ግድፈት እንዲሁም በክሶች እና እገዳ በውድድር አመቱ መነጋገርያ የሆነ ክለብ ሆኗል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ የአሰልጣኙን ምላሽ እና ቀጣይ ሁኔታ ተከታትላ ለአንባቢዎች የምታደርስ ይሆናል፡፡


© በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር ሙሉ ለሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ ፅሁፎቹን በሌላ ሚድያ ሲጠቀሙ ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *