ጋቦን 2017፡ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

ጋቦን በማስተናገድ ላይ ያለችው የ2017 ቶታል አፍሪካ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና ዕሁድ ቀጥለው ይረጋሉ፡፡ 

ከተወሰኑ ሃገራት በስተቀር አብዛኞቹ የሩብ ፍፃሜ ተፋላሚዎች ከምድባቸው አስቀድመው እንደሚያልፉ የተጠበቀ ነበር፡፡ አዘጋጅ ሃገር ከ1994 ወዲህ በማይኖርበት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች የተመልካች ቁጥር መቀነሱ ይቀጥላል፡፡ ለጨዋታ አመቺ ያልሆኑ ሜዳዎች በአብዛኛው ጋቦንን ሲያስተቻት ነበር፡፡

ማራኪ ግቦች፣ ያልተጠበቁ ውጤቶች፣ የማይታመኑ የግብ ጠባቂዎች ብቃት እንዲሁም በጋቦን መንግስት ላይ የሚሰሙ ተቃዎሞችን ያሳየን የአፍሪካ ዋንጫው ቅዳሜ 1፡00 ምሽት ላይ ቡርኪናፋሶ ከቱኒዚያ በማገናኘት የሩብ ፍፃሜው ይጀምራል፡፡ ቡርኪናፋሶ በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ጊኒ ቢሳውን 2-0 በማሸነፍ ምድብ አንድን በመሪነት በማጠናቀቅ ነው ለሩብ ፍፃሜው የበቃችው፡፡ ፈረሰኞቹ ወሳኝ ተጫዋቻቸውን ጆናታን ፔትሮፒያን በጉዳት ቢያጡም የፕሪጁስ ንኮልማ የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ለአሰልጣኝ ፓውሎ ዱራቴ መልካም የሚባል ዜና ነው፡፡ ቱኒዚያ ምድብ ሁለትን በሽንፈት ብትጀምርም በተከታይ በነበሩት ጨዋታዎች ድል ማድረጓ ከምድቡ አላፊ አድርጓታል፡፡ የነይም ሲሊቲ፣ የሱፍ ሳክኒ እና የዋሂብ ካዝሪ በድንቅ ብቃታቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ የአጥቂ መስመሩ ግን አሁንም አስተማማኝ አይደለም፡፡ አህመድ አኪያቺን እና ሳብር ካሊፋን የያዘው ቡድኑ ከአጥቂዎቹ ግብ እያገኘ አይደለም፡፡ በንፅፅር የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾቹ ለካርቴጅ ንስሮቹ ዋነኛ የግብ ምንጭ ሁነዋል፡፡ ቱኒዚያ በ2015 በሩብ ፍፃሜ ከተሰናበተችበት ውጤት የተሻለ ለማምጣት እንዲሁም ቡርኪናፋሶ ልክእንደ 2013 አስገራሚ ግስጋሴን ለማድረግ ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡

ዋንጫው ለማንሳት ከፍተኛ ግምት የተሰጣት ሴኔጋል ከካሜሮን ዛሬ ምሽት 4፡00 ላይ ይፋለማሉ፡፡ ሴኔጋል ጠንካራ የፊት መስመር ባለቤት መሆኗን በምድብ ጨዋታዎች አስመስክራለች፡፡ የቴራንጋ አንበሶቹ በመከላከሉም ረገድ ተሻሽለው ቀርበዋል፡፡ በምድብ ጨዋታዎች ያስተናገዱት የግብ መጠን ሁለት ብቻ ነው፡፡ ካሜሮን ከምድብ አንድ ሁለተኛ ሆኗ ነው ያጠናቀቀችው፡፡ የማይበገሩት አንበሶቹ እምብዛም ከዋክብትን ባይዙም ፍላጎት ያላቸው ተጫዋቾችን መያዛቸው ጠቅሟቸዋል፡፡ በ2002 የአፍሪካ ዋንጫ ካሜሮን አሸናፊ ስትሆን ሴኔጋልን በፍፃሜው ረታ ነበር፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የኃላ ታሪካቸው የሰፋ ልዩነት ቢኖራቸውም የአሁኑ የሴኔጋል ትውልድ ከካሜሮን በበለጠ አስፈሪ ነው፡፡ ዛሬም የካሜሮን የኃላ መስመር በሴኔጋል የአጥቂ መስመር እጅግ ይፈተናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዕሁድ ምሽት 1፡00 ላይ ከ2008 ወዲህ በአፍሪካ ዋንጫ ከግማሽ ፍፃሜ ቀርታ የማታውቀውን ጋናን እና ዲ.ሪ. ኮንጎን ያገናኛል፡፡ ጋና ከምድብ አራት ሁለተኛ ሆኗ ስታጠናቀቅ በሃገሯ ልጅ የምትመራው ኮንጎ ምድብ ሶስትን በአንደኝነት አጠናቅቃለች፡፡ ጋና አሳማኝ ያልሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ በምድብ ጨዋታ ላይ አሳይታለች፡፡ የአጥቂው አሰሞሃ ጂየን መጎዳት ከዚህ ጋር ተዳምሮ አሰልጣኝ አቭራም ግራንትን አስጨንቋል፡፡ ዲ.ሪ. ኮንጎ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል እያሳየ የመጣ ቡድን ነው፡፡ አሰልጣኝ ፎሎረንት ኢቤንጌ ያየዘው ስብስብ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማምራት የሚቸግረው አይመስልም፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው ኮከብ ግብ አግቢ ጁኒየር ካባናጋን የያዙት ነብሮቹ በምድብ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ተጋጣሚያቸው ጥቋቁር ከዋክብቶቹ ሁለት ግቦችን ከመረብ አዋህደዋል፡፡

ዕሁድ ምሽት 4፡00 ሁለቱ የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ግብፅ እና ሞሮኮ ይገናኛሉ፡፡ በ1998 አፍሪካ ዋንጫ በምድብ ጨዋታ ተገናኝተው የሙስጠፋ ሃጂ ግሩም ግብ የአትላስ አንበሶቹን አሸናፊ አድርጎ ነበር፡፡ አሁን ላይ ሃጂ የሃገሩ ብሄራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ነው፡፡ ከ2004 በቱኒዚያ በፍፃሜው ተሸንፋ ዋንጫ ካጣች በኃላ ሞሮኮ በአፍሪካ ዋንጫው ከምድብ ማለፍ ሲሳናት ታይቷል፡፡ አሁን ላይ በሄርቬ ሬናርድ እየተመራች ከምድብ ሶስት ኮንጎን ተከትላ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅላለች፡፡ በሚመርጡት የመከላካል አጨዋወት በፈርኦኖቹ ደጋፊዎች የሚተቹት ሄክቶር ኩፐር በአፍሪካ ዋንጫው አንድም ግብ ያላስተናገደ ቡድን መያዛቸው ያስወድሳቸዋል፡፡ ቡድኑ በእንቅስቃሴ የተሻለ የሚባል ባይሆንም በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ነው፡፡ የሞሮኮ ተጫዋቾች በራስ መተማመናቸው እየተሻሻሉ መምጣታቸው ግብፅን ሊያሰጋት ይችላል፡፡ በሁለቱ ሃገራት ቀደምት ግንኙነቶች ሞሮኮ የበላይነቱን ይዛለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *