መብራት ኃይል ሁለተኛውን ዙር በድል ጀመረ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር ቅዳሜ በቦዲቲ እና በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡

በ9 ሰአት ቦዲቲ ላይ በተደረገው የወላይታ ድቻ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ሳይሸናነፉ 1-1 አቻ ተለያይተዋል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ባለ ሜዳዎቹ ሲሆኑ በዝውውር መስኮቱ ከሐረር ቢራ የፈረመው አትክልት ንጉሴ ወላይታ ድቻን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቻ የምታደርገውን ግብ ያስቆጠረው የመስመር ተከላከዩ መሃሪ መና ነው፡፡ የአቻውን ውጤት ተከትሎ ወላይታ ድቻ በውድድር አመቱ ያስመዘገበው 10ኛ የአቻ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ባደረጉት የመጀመርያ ዙር ጨዋታ ወላይታ ድቻ 4-0 ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡

በአዲስ አበባ ስታድየም 11፡00 ላይ በተካሄደው የመብራት ኃይል እና የሀዋሳ ከነማ ጨዋታ መብራት ኃይል 2-1 አሸንፎ ከግርጌዎቹ ክለቦች በጥቂት ነጥቦች ርቋል፡፡

ሀዋሳ ከነማ የቀድሞው የመብራት ኃይል ኮከብ ታፈሰ ተስፋዬ ባስቆጠረው ግብ መምራት ቢችሉም ከእረፍት መልስ በመልካም አቋም ላይ የሚገኘው አብዱልከሪም ሃሰን እና በመጀመርያው ዙርም ሀዋሳ ላይ የአሸናፊነቱን ግብ ያስቆጠረው ተሾመ ኦሼ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦች የማይዘሙት ምሰሶዎች 3 ነጥብ ይዘው ወጥተዋል፡፡ ድሉ ለመብራት ኃይል ከወራጅ ቀጠና ለማምለጥ ስንቅ የሆነ ሲሆን በተቃራኒው ለ5ኛ ተከታታይ ጨዋታ ሽንፈት የደረሰበት ሀዋሳ ከነማ ከመሪዎቹ ተርታ ወርዶ ወደ ወራጅ ቀጠናው እያዘገመ ነው፡፡

ሊጉ ዛሬም ሲቀጥል ይርጋለም ላይ ሲዳማቡና ከ መከላከያ ፣ አርባ ምንጭ ላይ አርባ ምንጭ ላይ አርባ ምንጭ ከነማ ከ ኢትዮጵያ መድን ፣ ሐረር ላይ ሐረር ቢራ ከ ዳሽን ቢራ በተመሳሳይ በ9፡00 አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሙገር ሲሚንቶ 11፡00 ላይ ይጫወታሉ፡፡

{jcomments on}

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *