ዝውውር | አዲስ አበባ ከተማ 4 የውጪ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

አዲስ አበባ ከተማ የኮንጎ ፣ ማሊ እና ጋና ዜጋ የሆኑ 4 ተጫዋቾችን እንዳስፈረመ የቡድኑ አሠልጣኝ ስዩም ከበደ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። ተጫዋቾቹ በአንድ አመት ኮንትራት ነው ክለቡን የተቀላቀሉት፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተወላጅ የሆነው ሲና ጄሮም የ27 ዓመት የአጥቂ አማካይ ሲሆን በሀገሩ ሊግ ለዲሲ ቪሩንጋ እና ሴንት ኤሎይ ሉፖፖ ክለቦች ተጫውቷል። በ2012 መጨረሻ ወደ ሩዋንዳ በማቅናት ለፖሊስ ክለብ የፈረመው ጄሮም ለሌላው የሩዋንዳ ክለብ ራዮን ስፖርትም ተሰልፎ መጫወት ችሏል። ተጫዋቹ በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ረጅም ጊዜን በማሳለፉ የሩዋንዳ ዜግነት አግኝቶ የብሔራዊ ቡድኑን ማልያ በመልበስ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ለዩጋንዳው ኤስሲ ቪላ ክለብ ፈርሞ የነበረው ጄሮም በቅድመ ውድድር ዘመን እና የዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ላይ ግቦችን አስቆጥሯል።

ሲና ጄሮም (ሰማያዊ መለያ)

የ30 ዓመቱ ማሊያዊ አጥቂ ማካን ዴምቤሌ ሌላው ለአዲስ አበባ ከተማ የፈረመ ተጫዋች ነው። ዴምቤሌ የዩኤፍኤኤስ ባማኮ ወጣት ቡድን ፍሬ ሲሆን በሰሜን አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ክለቦች ለረጅም ጊዜ የመጫወት ልምድ ያለው ተጫዋች ነው። ተጫዋቹ በኢራን ክለቦች ጎስታሬሽ ፉላድ፣ አቦሞስሌም እና ባንዳር አባስ ክለቦች መጫወት የቻለ ሲሆን በአፍሪካ መድረክ ትልቅ ስም ባላቸው የሞሮኮው ራጃ ካዛብላንካ እና የአልጄሪያው ጄኤስ ካባልዬ ተጫውቶ አሳልፏል። ዴምቤሌ በ2013 ወደ ትውልድ ሃገሩ ማሊ ከተመለሰ በኋላ በልጅነት ክለቡ ዩኤፍኤኤስ ባማኮ እና በሌላው የማሊ ፕሪሜራ ዲቪዥን ክለብ ኤኤስ ፖሊስ ሁለት አመታትን አሳልፏል።

ማካን ዴምቤሌ

ጋናዊው የቀድሞ የአክራ ኸርትስ ኦፍ ኦክ አጥቂ ጄምስ ክዋሜ አባን በኢራቅ ሊግ ከሚጫወተው አል ታላባ አዲስ አበባ ከተማን ተቀላቅሏል። የ28 ዓመቱ አጥቂ በተወለደበት ተማሌ ከተማ ውስጥ ላለው የጋና 2ኛ ዲቪዝዮን ክለብ ሌፖ ስታርስ በመጫወት የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረ ሲሆን በ2009/2010 የጋና ፕሪምየር ሊግ 8 ለግሬት ኦሎምፒክስ በመጫወት 8 ግቦችን አስቆጥሮ ከሊጉ ከፍተኛ ግብ አግቢዎች ተርታ መሰለፍ ችሎ ነበር። ተጫዋቹ በጋና ከኸርትስ ኦፍ ኦክ በተጨማሪ ሊበርቲ ፕሮፌሽናልስ፣ ዋ ኦል ስታርስ እና አዱዋና ስታርስ ክለቦች ቆይታ ነበረው። ጄምስ አባን በ2011 በቻይና ሼንዘን በተደረገው የዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ላይ ሃገሩ ጋናን በመወከል ተሳትፏል።

ጄምስ ክዋሜ አባን

የጋና ሁለተኛ ዲቪዝን ክለብ በሆነው እና በቀድሞው የጋና ታላቅ ተጫዋች አቢዲ ፔሌ የሚመራው ኤፍሲ ናኒያ ተጫዋች የነበረው አሊ አያና አራተኛው የአዲስ አበባ ከተማ ፈራሚ ነው።

በ13 ጨዋታዎች 8 ነጥቦችን ይዞ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ እነዚህን ተጫዋቾች ማስፈረሙ ቡድኑን የተሻለ ተፎካካሪ የሚያደርግ እና በሁለተኛው ዙር ወደ ከፍተኛ ሊጉ ላለመውረድ ለሚያደርገው ትግል ጠንካራ ስብስብ ይዞ እንዲቀርብ የሚረዳው ይሆናል።


© በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር ሙሉ ለሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ ፅሁፎቹን በሌላ ሚድያ ሲጠቀሙ ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *