ፕሪሚየር ሊግ ፡ የሸገር ደርቢ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአዲስ አበባ ባላንጣዎች ፍልሚያ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል የግብ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከ25ኛው ደቂቃ በኋላ ጫና ፈጥረው መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ የጨዋታ የበላይነት ያሳየው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ60ኛው ደቂቃ ብሪያን ኡሞኒ ከበኃይሉ አሰፋ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠራት ግብ 1-0 መምራት ችለዋል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በሃይሉ አሰፋ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 እነዲመራ ያስቻለችውን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በውጥረት በተሞላው ጨዋታ የእለቱ አርቢቴር በአምላክ ተሰማ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ በበሃይሉ አሰፋ ላይ የተፈፀመውን ጥፋት በዝምታ በማለፉ ተቃውሞን ያስተናገደ ሲሆን በካታንጋ አካባቢም በደጋፊዎች መካከል ግጭት ተስተውሏል፡፡

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ውጤቱ የተጫዋቾቹ የጥረት ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ በመጀመርያው አጋማሽ እንዳሰብነው ብንንቀሳቀስም ስህተቶችም ሰርተናል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የቡናን ክፍተቶች ለመጠቀም ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልን አሸንፈን ወጥተናል፡፡ እንደጨዋታ እንቅስቃሴያችን እና የፈጠርናቸው እድሎች ማሸነፋችን ተገቢነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ትኩረታችን ዋንጫው ላይ እንደመሆኑ በየጊዜው የምንሰራቸውን ስህተቶች እያረምን ከፊታችን ያሉትን ጨዋታዎች በብቃት እንወጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ አንዋር ያሲን በበኩላቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫቸውን ወደ ግብ አለመቀየራቸው ለሽንፈት እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ በመጀመርያው 45 ጨዋታውን ብንቆጣጠርም ግቦች ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ ተጋጣሚያችን ያገኙትን የግብ አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀማቸው አሸንፈውናል፡፡ የመረጥነው የጨዋታ ሲስተም ኳሱን እንደልብ እንድንጫወት ቢያደርገንም በ3 ተከላካይ የተዋቀረው የተከላካይ ክፍላችን በቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎች የቁጥር ብልጫ እንዲወሰድብን አድርጎናል፡፡ ይህም በሁለተኛው አጋማሽ ወደ 4 ተከላካዮች እንድንመለስ አስገድዶናል›› ብለዋል፡፡

ድሉን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ38 ነጥብ መሪነቱን ሲያስጠብቅ ከ1993 ወዲስ በሁለቱም ዙሮች ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ የተሳነው ኢትዮጵያ ቡና በነበረበት 4ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል፡፡

ያጋሩ