በቶታል 2017 የአፍሪካ ዋንጫ ጋና እና ግብፅ የሩብ ፍፃሜ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት የመጨረሻ አራቱን የተቀላቀሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ግብፅ ከ31 ዓመታት ቆይታ በኃላ ሞሮኮን ስታሸንፍ ጋና ዲ.ሪ. ኮንጎን በአዩ ወንድማማቾች ግብ ታግዛ ረታለች፡፡
በሰሜን ጋቦን ከተማ ኦየም በተደረገው ጨዋታ ጋና ዲ.ሪ. ኮንጎን 2-1 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለተከታታይ ስድስተኛ ግዜ አምርታለች፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ዕምብዛም ሙከራዎች ባልታዩበት ግጥሚያ ጥቋቁር ከዋክብቶቹ የኳስ ቁጥጥር የበላይ ነበሩ፡፡ ቢሆንም ነብሮቹ በዱመርሲ ሞቦካኒ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር፡፡ የጋናን ግብ ጠባቂ ራዛክ ብሪማን ያለፈው ሞቦካኒ ሙከራው የግቡን ቋሚ ነበር የመለሰበት፡፡ በ63ኛው ደቂቃ ጆርዳን አዩ ባስቆጠረው ግብ መምራት ችለዋል፡፡ ጆርዳን ከሙባረክ ዋካሶ ያገኘውን ኳስ አንድ የኮንጎን ተከላካይ በማለፍ በመልካም አጨራረስ ጋናን መሪ አድርጓል፡፡ ፖል ሆዜ ፖኩ ኮንጎን አቻ የምታደርግ ግብ ከርቀት አክርሮ በመምታት ቢያስቆጥርም የግራ ተመላላሹ ጆይስ ሎማሊሳ ክሪስቲያን አትሱ ላይ በፈፀመው ጥፋት ምክንያት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አንድሬ አዩ ከመረብ አዋህዷ የጋናን ግስጋሴ አስቀጥሏል፡፡ የኮንጎው አሰልጣኝ ፍሎረንት ኢቤንጌ የአቻነት ግብ ፍለጋ አራት አጥቂዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ በተለያ ብሪማ የሲድሪክ ባካምቦን ጠንካራ ምት በመመለስ ወሳኝ ሚናን ተወጥቷል፡፡ ጋና ለስድስት ተከታታይ ግዜ ለግማሽ ፍፃሜው ስትደርስ ከ1982 ወዲህ ያጣችውን የአፍሪካ ዋንጫ ክብርን ለማግኘት አልማለች፡፡ የአዩ ቤተሰብ (አቢዲ ፔሌ አዩ፣ ክዋሜ አዩ፣ አንድሬ አዩ እና ጆርዳን አዩ) በአፍሪካ ዋንጫው 16 ግቦችን በጋራ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ክዋሜ አዩ የአቡዲ ፔሌ ወንድም ነው፡፡ ጆርዳን አዩ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
ግብፅ የ31 ዓመታት በኃላ ሞሮኮን ማሸነፍ በቻለችበት ጨዋታ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ግማሽ ፍፃሜ አድርሷታል፡፡ በፖር ዠንቲል በተካሄደው የሰሜን አፍሪካዎቹ ፍልሚያ የአትላስ አንበሶቹ በሙከራ ረገድ ከፈርኦኖቹ ተሸለው ቢታዩም ግብ ለማስቆጠር ግን አልቻሉም፡፡ የሙባረክ ብሶፋ ሙከራ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ከሙከራዎቹ መካከል የምትጠቀስ ነች፡፡ የጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው መሃሙድ ካራባ የግብፅን ማሸነፊያ ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ካራባ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ሲገጭ የቡድን አጋሩ አህመድ ኮካ ቢደረብም ዳግም የመጣውን ኳስ ከቅርብ ርቀት ወደ ግብነት ቀይሯል፡፡ ግብፅ በ2010 በኃላ እየተሳተፈችበት በሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫ አንድም ግብ አላስተናገደችም፡፡ ፈርኦኖቹ ለመጨረሻ ግዜ ሞሮኮን ያሸነፉት በ1986ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ ከ1986 በኃላ በነበሩ 12 ግንኙነቶች በአራቱ ሞሮኮ ስታሸንፍ 8 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል፡፡ ግብፅን እና ሞሮኮ በ1986፣ 1998 እና 2006 የአፍሪካ ዋንጫዎች የተገናኙ ግብፅ የውድድሮቹ አሸናፊም ሁናለች፡፡ መሃሙድ ካራባ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ ተመርጧል፡፡
በግማሽ ፍፃሜው ቡርኪናፋሶ ከግብፅ እንዲሁም ጋና ከካሜሮን ይጋጠማሉ፡፡ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ ዕረቡ እና ሐሙስ በሊበርቪል እና ፍራንስቪል ይደረጋሉ፡፡ ዕረቡ ምሽት 4፡00 ቡርኪናፋሶ ከግብፅ እንዲሁም ሐሙስ በተመሳሳይ ሰዓት ካሜሮን ከጋና ይጋጠማሉ፡፡
የፎቶ ምንጮች፡ AFP & BackpagePix