​የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ንግድ ባንክን በመርታት ደረጃውን ማሻሻሉን ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ሲጀምር ኢትዮጵያ ቡና በጎል ተንበሽብሿል፡፡ ቡናማዎቹ የውድድር አመቱን ድንቅ አቋም ባሳዩበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 5-2 በመርታት ደረጃውን ማሻሻሉን ቀጥሏል፡፡

ቀደም ሲል 11:30 በአዲስ አበባ ስታድየም  እንዲካሄድ ፕሮግራም ወጥቶለት የነበረው ይህ ጨዋታ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ምክንያት ወደ አበበ ቢቂላ ስታድየም ተዛውሮ 10:00 ላይ ተደርጓል፡፡ ደጋፊዎችም የለውጡን ዜና ዘግይተው የሰሙ በሚመስል መልኩ ስታድየሙ በተመልካች ለመሞላት ጨዋታው ከጀመረ በኋላ እስከ ግማሽ ሰአት ፈጅቶ ነበር፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መውሰድ ቢችልም በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች አደጋ የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ አልቻሉም ነበር፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ ብልጫቸውን ወደ ተደጋጋሚ ግብ ሙከራዎች መቀየር ችለዋል፡፡ በተለይም ባልተለመደ ሁኔታ በቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው  ቢንያም ሲራጅ የሚፈጥረውን ክፍተት በመጠቀም ሳሙኤል ሳኑሚ እና አስቻለው ግርማ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ እያጠበቡ በመግባት አደጋ መፍጠር ችለዋል፡፡

በ31ኛው ደቂቃ ናይጄርያዊው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ ከጋቶች ፓኖም የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ 

ከግቡ መቆጠር በኋላ ቀሪዎቹ የመጀመርያው አጋማሽ ደቂቃዎች ከመሃል ሜዳ ያልዘለለ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ አሳይቶ በኢትዮጵያ ቡና 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና እጅግ ተሻሽሎ መቅረብ ሲችል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ተዳክሞ ታይቷል፡፡ በተለይም የተከላከዮች ትኩረት ማጣት እና ተደጋጋሚ ስህተት ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል፡፡
በ49ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ኤልያስ ማሞ ያቀበለውን ኳስ አስቻለው ግርማ በቀላሉ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂውን አልፎ የኢትዮጵያ ቡናን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡ 

ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላ ነገሮች ለኢትዮጵያ ቡና አልጋ በአልጋ ሆነውለታል፡፡ በዚህም በ5 ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ኤልያስ ማሞ በድጋሚ በ57ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ለአስቻለው ያቀበለውን ኳስ ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ተቆጣጥሮ የኢትዮጵያ ቡናን መሪነት ወደ 3 ከፍ ያደረገበትን ጎል በምርጥ አጨራረስ ሲያስቆጥር ከአምስት ደቂቃ በኋላ በሳሙኤል ሳኑሚ ላየይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ጋቶች ፓኖም አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ 4-0 አስፍቶታል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቡና ምላሽ ለመስጠት እስከ ጨዋታው የመጨረሻ 20 ደቂቃ ድረስ ለመጠበቅ ተገዷል፡፡ በ72ኛው ደቂቃ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቡና የመጀመርያ አሰላለፍ የተካተተው አክሊሉ ዋለልኝ ሳጥኑ ውስጥ ኳስ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ናይጄርያዊው ፒተር ኑዋዲኬ አስቆጥሮ ውጤቱን ወደ 4-1 አጥብቧል፡፡ 

በ85ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳኑሚ ከባንክ ተከላካዮች የነጠቀውን ኳስ ተጠቅሞ በግብ ጠባቂው አናት “ቺፕ” በማድረግ የቡናን መሪነት መልሶ ወደ 4 አስፍቷል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን ከቀላቀለ ወዲህ ባሳየው የአቋም መውረድ ወደ ተጠባባቂ ወንበር ወርዶ የነበረው እና ክለቡን በውሰት ለመልቀቅ ተቃርቦ የነበረው ሳኑሚ በ2 ጨዋታ 3 ግቦች በማስቆጠር ወደ ቀድሞ አቋሙ መመለሱን እያሳየ ይገኛል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አምሀ በለጠ በ87ኛው ደቂቃ ፒተር ኑዋዲኬ የመታውን ኳስ ሀሪስን ሲተፋው አግኝቶ የንግድ ባንክን የግብ እዳ ከመቀነስ ያልዘለለ ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ጨዋታው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን ከተጀመረ ወዲህ በአንድ ጨዋታ የተመዘገበ ከፍተኛ የጎል መጠን ሲያስተናግድ ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ከመጥፎ አጀማመሩ በማንሰራራት በ23 ነጥቦች ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ በ13 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

*ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ በእጅ የነካው አክሊሉ ዋለልኝ ሳይሆን ኤፍሬም ወንድወሰን በሚል እንዲስተካከል ከይቅርታ ጋር እንገልጻለን፡፡ 

2 Comments

  1. በጣም በጣም ጐበዝ ናቸሁ በርቱ ቀጥሉበት ግን ከጫወታ በፊት ግምታዊ አስተላለፍ ግምታዊ ውጤቶች በተለያዩ እንግዶች(ባለሙያዎች) ብታቀርቡ፡፡ቅድሜ ግምታዊ ግምት የጫዎታ ዉጤቶች ለአንባብዎች ብታቀርቡ፡፡ የእለቱን የጫዎታ ኮከብ ተጫዋች የወሩን ብታስመርጡን፡፡
    በተረፈ በጣም ተምችቶናል በርቱ፡፡

Leave a Reply