ሀዋሳ ከተማ በክለቡ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል

ሀዋሳ ከተማ በክለቡ ወቅታዊ ጉዳዩች ዙርያ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ የሚድያ አካላት በተገኙበት ዛሬ ተካሂዷል፡፡ የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ እና የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ታምሩ ታፌ እንዲሁም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡ ሲሆን ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም እንዲህ ባለ መልኩ አሰናድታዋለች፡፡

” ሀዋሳ ከተማ የሚገኝበት ደረጃ የሚመጥነው አይደለም” አቶ ታምሩ ታፌ

ስለ ክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ

ክለቡ አሁን ያለበት ደረጃ ጥሩ አይደለም፡፡ ይህም ሀዋሳ ከተማ ከነበረው ስም አኳያ የሚመጥነው አይደለም፡፡ እዚህ ላይ አስምሬ መናገር የምፈልገው ሀዋሳ ከተማ ያለበት ደረጃ አይመጥነው እንጂ ወደ ታችኛው ሊግ በፍጹም አይወርድም፡፡ ይሄ እግር ኳስ ነው በእግር ኳስ ከሚያጋጥሙት ነገሮች አንዱ ይህ ነው፡፡ በቡድናችን ድክመት ዙርያ 12 ሰአት የፈጀ ግምገማ አድርገናል፡፡ በግምገማችንም የአንዳንድ ተጫዋቾች ከአሰልጣኙ ጋር ያለመግባባት ችግር ለውጤት ማጣታችን እንደ መንስኤ አንስተናል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የጉዳት እና ቅጣት መደራረብ እንዲሁም ዘንድሮ ከወጣት ቡድን ያደጉት ተጫዋቾች ልምድ ማነስ ዋጋ እንዳስከፈለን በግምገማችን አረጋግጠናል፡፡

 

ስለተጫዋቾች ጥራት

አብዛኛዎቹ ተጫዋቾቻችን ከተስፋ ያደጉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከነባሮቹ ጋር ተዋህደው ጥሩ ውጤት በማምጣት አሁን ካለንበት ችግር እንላቀቃለን ብዬ አሰባለው፡፡

ወደ አሸናፊነት መመለስ

ክለባችን ጨዋታ የመቆጣጠር ችግር የለበትም፡፡ እኛ ውጤት የምናጣው በመጨረሻወቹ ደቂቃዎች በሚቆጠሩብነ ግቦች እና መሪነታችንን አስጠብቀን እንድንወጣ የሚረዳን ተከላካይ እጦት ነው ዋጋ እንድንከፍል ያደረገን፡፡ ይህን ለማረም እየሰራን እንገኛለን ይህም ተጫዋቾች ግብ ለማስቆጠር ካላቸው ጉጉት በመነሳት መከላከሉን በመዘንጋት ነው፡፡ ለምሳሌ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መከላከያ ፣ አዳማ ከተማ እና ወልድያ በፍፁም መሸነፍ የሌሉብን ጨዋታዎች ነበሩ፡፡

የተጫዋቾች ስነ ምግባር ጉድለት

ለውጤታችን መጥፋት የተጫዋቾች ስነ ምግባር ጉድለት አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በቀይ እና በሌላ ምክንያት የሚወጡ ተጫዋቾች ክፍተት ለሽንፈታችን ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ በዲሲፕሊን ግድፈት ሶስት ተጫዋቾች ቀጥተን ነበር፡፡ ያልተገባ ባህሪ ማሳየት እና ስሜታዊ መሆን በፍጹም የለብንም ፤ ይህ መስተካከል እንዳለበት በግምገማችን አረጋግጠናል፡፡ ከአሁን በኃላ ለክለቡ እንጂ ስግለሰብ አሳቢ መሆን የለብንም፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ ላይ ስለሚነሳው ተቃውሞ

እኛ ከዚህ ቀደም እንደተናገርነው በአሰልጣኝ ውበቱ ላይ ትልቅ እምነት አለን፡፡ ታላቅ አሰልጣኝ ነው፡፡ የተዘነጋውን ታዳጊዎችን ወደ ዋናው ቡድን የማሳደግ ስራ ዳግም በውበቱ እያየን ነው፡፡ ውጤቱ አስከፊ ቢባልም ይህ ውበቱንና ክለቡን አይገልፅም፡፡ ተጫዋቾቹ እና አሰልጣኝ ውበቱ የነበረባቸው ያለመግባባት አሁን ተፈቷል፡፡ አሁንም ያኔ ካለንበት የውጤት ችግር እንዳወጣን አሁንም ዳግም ያወጣናል፡፡

ስለደጋፊው

ሀዋሳ ከተማ ትልቅ ክለብ ነው፡፡ ስለ ሀዋሳ የሚያውቁ ያለበት ደረጃ አይመጥነውም፡፡ አንዳንድ ክለቡን የሚጠሉ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ክለብ የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ክለብ ነው፡፡ ለደጋፊዎቹ የተሻሉ ነገሮች ማልያ ለመሰራት ታስቧል፡፡ 5 ያህል ስፖንሰርም አግኝተናል፡፡ ይህን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን ፡፡

ስለ ፍሬው ሰለሞን

በድሬዳዋው ጨዋታ ያሳየው ባህሪ ያልተገባ ነበር፡፡ ስለዚህ ላጠፋው ጥፋት ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡

“ደጋፊው ሊታገሰን ይገባል” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

ስለ ክለቡ

ከሚቆጠርብን በላይ እያስቆጥረን መውጣት አለብን፡፡ እስካሁን ትንንሽ ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ ከ1ኛው ዙር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራን ነው፡፡

የስነ ልቦና ችግር ተጫዋቾቼ ላይ ይታያል፡፡ ይህም ተደጋጋሚ ሽንፈቶች ያመጡት ነው፡፡ ውስጣችን ንፁህ ከሆነ እና አንድ ከሆንን እንዲሁም የራሱን ኃላፊነት ከተወጣ ክለቡን መታደግ ይቻላል፡፡

ስለ ክለቡ ደጋፊዎች

ደጋፊው ሊታገሰን ይገባል፡፡ ክለቡን እንጂ ግለሰብ መደገፍ የለብንም ፤ ካለው የውጤት መጥፋት አንጻር ደጋፊዎች እኔን ቢቃወሙ አይገርመኝም፡፡ ነገር ግን ደጋፊዎች ውጤታማ በሆንበት ብቻ ሳይሆን ውጤት በምናጣበትም ወቅት ከጎኛችን ሊሆኑ ይገባል፡፡ አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችንም ማበረታታት ከደጋፊዎቹ ይጠበቃል፡፡

ስለ ሳሙኤል ሳኑሚ

ኢትዮጵያ ቡና ሳኑሚን በውሰት ሰጥቶናል፡፡ አሁን ግን ተጫዋቹን እንደማይለቁት በመግለፃቸው ውዝግብ ተከስቷል፡፡ በህጋዊ ደብዳቤ እና ተጫዋቹ እኛ ጋር  እንደሚጫወት ፈርሞ አረጋግጧል፡፡ ፌድሬሽኑም ቡና በውሰት ለመስጠት ፍቃደኛ የሆነበት ደብዳቤ ደርሶታል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን ተከታትለን ለማስፈፀም እየታገልን ነው፡፡

በቀጣይ. . .

ቀጣይ ሁሉም የተሻለ ነገር ይጠብቃል፡፡ እኛም ክለቡን ካለበት እናወጣዋለን፡፡ ከሚዲያው እና የክለቡ አመራሮች ጋር በጋራ ሆነን ጉድለታችንን እየሞላን ክለቡን ጥሩ ደረጃ እናደርሰዋለን ብዬ አሰባለው፡፡ ተጫዋቾቼም ለማለያ ፍቅር ሲሉ የሚችሉትን ማድረግ አለባቸው፡፡

ስለፍሬው ሰለሞን

ፍሬው የሰራው ተግባር መጥፎ ነው፡፡  እኔንም አላከበረም ፤ ልምድ ያለው ተጫዋች በመሆኑ አርአያ መሆን እንጂ እንዲህ አይነት ተግባር ማድረግ የለበትም፡፡ ሁሉም ከሱ ስህተት ሊማሩ ይገባል፡፡ በእግር ኳስ ከመዝናናት ባሻገር መከባበርን ልንማር ይገባል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *