ፕሪሚየር ሊጉ የአንድ ፈረስ ሩጫ እየመሰለ ነው

ቅዳሜ የተጀመረው የፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ዙር ትላንት በተካሄዱ 4 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ድል ቀንቷቸዋል፡፡

ይርጋለም ላይ መከላከያን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 2-0 አሸንፎ በቅርብ ጊዜ መልካም አቋሙ ቀጥሎበታል፡፡ ለሲዳማ ቡና የማሸነፍያዎቹን ግቦች የመከላከያው ተካለካይ ተስፋዬ በቀለ በራሱ ግብ ላይ እና የመስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሃመድ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

የይርጋለሙ ክለብ በአመቱ አመዛኝ ሳምንታትን በወራጅ ቀጠና ሲያሳልፉ ቆይተው በቅርብ ጨዋታዎች በግሩም ሁኔታ እያንሰራሩ መጥተዋል፡፡ በአንጻሩ አመቱን በድንቅ ሁኔታ የጀመሩት መከላከያዎች በሊጉ የመጨረሻ ድላቸውን ካስመዘገቡ 6 ጨዋታዎች አልፈዋል፡፡

በአዲስ አበባ ስታድየም ሙገርን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀላሉ 4-0 አሸንፎ መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ ለፈረሰኞቹ የድል ግቦቹን አበባው ቡታቆ እና ፍጡም ገብረ ማርያም አንድ ኡመድ ኡኩሪ ደግሞ ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል፡፡ ኡመድ ኡኩሪ ከመረብ ያሳረፋት ግሩም ግብ ፍጥነት እና ጥንካሬ ከተመልካቾች አድናቆት አስገኝታለታለች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሉን ተከትሎ የደረጃ ሰንጠረዡን በ39 ነጥብ ሲመራ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ኢትዮጵያ ቡና በ11 ፣ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ካለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ በ15 ነጥቦች ርቆ ተቀምጧል፡፡

ሐረር ላይ ዳሽን ቢራን ያስተናገዱት ሐረር ቢራዎች ሙሉ 90 ደቂቃውን ቢንያም ኃይሉ ባስቆጠረው ግብ 1-0 ሲሩ ቆይተው በተጨማሪ ሰአት ለዳሽን ግቧን ያስቆጠረው ቢንያም ኃይሉ በራሱ መረብ ላይ ባስቆጠረው ግብ 1-1 አቻ ተለያይተዋል፡፡ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ከኢትዮጵያ መድን ካለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ 14ኛ ሳምንት ማክሰኞ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ቡና ከ ደደቢት በአዲስ አበባ ስታዲየም 11፡30 ላይ ይፋለማሉ፡፡

ያጋሩ