የጨዋታ ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ከ10 ጨዋታ በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

በ14ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ጅማ አባ ቡናን 2-1 በመርታት በአመቱ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡

የሀዋሳ 2ኛ አምበል ፍሬው ሰለሞን ለደጋፊዎች እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አበባ በማበርከት ነበር የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የተጀመረው፡፡

ሀዋሳ ከተማ እንደተለመደው የኳስ የበላይነት ባሳየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ኳሶችን ሲያመክን ተስተውሏል፡፡

ጃኮ አረፋት ከዳንኤል እና ደስታ የተሻገሩለትን ኳሶች ሳይጠቀምባቸው የቀረው እንዲሁም ዮናታን ከበደ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ ሀዋሳዎች በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች የፈጠሯቸው የግብ እድሎች ነበሩ፡፡

ጅማ አባቡናዎችም በረጅም ኳሶች በመጠቀም በአሜ መሀመድ እና መሀመድ ናስር አማካይነት ሙከራወችን አድርገዋል፡፡ በፈጣን እንቅስቃሴ የሚታወቀው አሜ መሀመድ ወደ ግብ ምክሮ ከግቡ ጫፍ ላይ መላኩ ወልዴ ያወጣት ኳስም ጅማወች ወደ ጨዋታው ሪትም እንዲገቡ ያደረገች ነበረች፡፡

የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ተጨማሪ አንድ ደቂቃ በቀረበት ወቅት መሀመድ ናስር ሞክሮ በሀዋሳ ተከላካይ ስህተት ስትመለስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አሜ መሀመድ አባ ቡናዎችን ቀዳሚ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አቅንተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም ሀዋሳ ከተማ የበላይነት ማሳየቱን ቀጥሏል፡፡ በጅማ አባቡና በኩል ደግሞ ተጠቃሽ ሙከራዎች ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በተለይም ዳዊት ተፈራ በጉዳት ሲወጣ የጅማ የመሀል ክፍል እንዲሳሳ ምክንያት ሆኗል፡፡

በ59ኛው ደቂቃ ደስታ ዩሀንስ ወደ ሳጥን  እየገፋ ሲገባ ተከላካዩ ቢያድግልኝ ኤልያስ በመጥለፉ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን አሰቆጥሮ ሀዋሳን አቻ አድርጎል፡፡

ሀዋሳዎች ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል፡፡ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው ጋዲሳ መብራቴም በተደጋጋሚ ከርቀት አክርሮ በመምታት የጅማን በር መፈተሽ ችሏል፡፡

ጋዲሳ መብራቴ በ67ኛው ደቂቃ ላይ ተደጋጋሚ ሙከራው ፍሬ አፍርቶለት ከ25 ሜትር ርቀት አክርሮ የመታት ኳስ በግሩም ሁኔታ ጅማ መረብ ላይ አርፋለች፡፡

ሀዋሳ ከተማ በዳንኤል ፣ ኤፍሬም እና አረፋት አማካኝነት ተጨማሪ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን ባያመክኑ የግብ መጠኑ ከዚህም በሰፋ ነበር፡፡ በተለይም ጋዲሳ መብራቴ ከርቀት ያሻገረውን ኳስ ጃኮ አረፋት ወደ ግብ መቶ የግቡን ቋሚ ነክታ የወጣችው የመጨረሻ ደቂቃ ሙከራ አስደንጋጭ ነበረች፡፡

ውጤቱ ሁለቱን ቡድኖች በደረጃ ሰንጠረዡ ቦታ ያቀያየረ ሆኗል፡፡ ከ10 ተከታታይ ጨዋታ በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ሀዋሳ ወደ 14ኛ ከፍ ሲል አባ ቡና ወደ 15ኛ ዝቅ ብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *