​የጨዋታ ሪፖርት | የምንተስኖት አዳነ ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስን በሰንጠረዡ አናት ላይ አቆይቶታል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ጨዋታቸውን ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ከተማ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግርጌ ላይ ከሚገኘው አአ ከተማ ከባድ ፈተና ደርሶበት በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ከሽንፈት አምልጧል፡፡

የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ የሚል እንቅስቃሴ ታይቶበታል፡፡ በተለይም በመጀመርያዎቹ 30 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች የግብ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡

40ኛው ደቂቃ ላይ ኃይሌ እሸቱ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከዋለው ከነአን ማርክነህ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ አዲስ አበባ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በአአ ከተማ መሪነት ተገባዷል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግልጽ የግብ እድሎች ያልፈጠረለትን ጫና በአአ ከተማ ላይ ማሳደር ችሏል፡፡ በተለይም ወጣቱ ጊት ጋት በ50/50 ኳሶች እና የተሳኩ ሸርተቴዎች የፈረሰኞቹ አጥቂዎችን የተቆጣጠረበት መንገድ አስገራሚ ነበር፡፡ አአ ከተማዎች በበኩላቸው በጥብቅ መከላከልና በመልሶ ማጥቃት ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ሲደርሱና ከሳጥን ውጪ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ተስተውሏል፡፡ አምበሉ ሙሃጅር መኪ ከመስመር እየተነሳ የሚፈጥራቸው እድሎች እና ከርቀት የሚሞክራቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡
የጨዋታው ሰአት እየገፋ በሄደ ቁጥር ቅደስ ጊዮርጊስ የአጥቂ ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት በተሻጋሪ ኳሶች ጫናውን አጠናክሮ ሲቀጥል አአ ከተማም የተከላካዮችን ቁጥር በማብዛት በጠንካራ መከላከል እስከመገባደጃ ደቂቃዎች መዝለቅ ችለው ነበር፡፡ 

በ89ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ምንተስኖት አዳነ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ግቧ ከመቆጠሯ በፊት ምንተስኖት በጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ይገኝ ነበር በሚል የአአ ከተማ ተጫዋቾች ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ከአቻነቱ ግብ በኋላም በቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ሙሃጅር መኪ በመውደቁ አአ ከተማዎች የፍጹም ቅጣት ምት ይገባናል ቢሉም ዳኛው ለሙሃጅር የማስጠንቀቂያ ካርድ መስጠታቸው አዲስ አበባዎችን አስቆጥቷል፡፡ 

ውጤቱ ሁለቱም ቡድኖች ባሉበት ደረጃ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተፎካካሪዎቹ ነጥብ መጣልን ተከትሎ አሁንም በሊጉ መሪነት ሲቆይ አዲስ አበባ ከተማም በ9 ነጥቦች የሊጉ ግርጌ ላይ ቆይቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *