የጨዋታ ሪፖርት | ድሬዳዋ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል አስመዝግቧል 

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛው ሳምንት ዛሬ ድሬዳዋ ላይ ድሬደዋ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው እስካሁን ካደረጋቸው ጨዋታዎች በተሻለ ቁጥሩ በርካታ የሆነ ተመልካች የታደመ ሲሆን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የፋሲል ከተማ ደጋፊዎችም በስታዲዮሙ የተለያዩ ቦታዎች ተሰባስበው ክለባቸውን ሲደግፉ ታይተዋል፡፡

ጨዋታው ጥንቃቄ የተሞላበት ፣ በጎል ሙከራ ያልታጀበ ፣ በተደጋጋሚ ፊሽካ ጨዋታው የተቆራረጠበት ፣ አከራካሪና አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ የታየበት ሆኖ አልፏል፡፡

ፌዴራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ባስጀመሩት ጨዋታ ገና በመጀመርያው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ለማ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ ወደ ጎልነት በመቀየር ድሬዳዋዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ ባሉት ደቂቃዎች አፄዎቹ በተወሰነ መልኩ በጎሉ መቆጠር ሲረበሹ ድሬዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡

ፋሲሎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት አጋጣሚ ጨዋታው ተጋግሎ ቀጥሎ በተለይ 23ኛው ደቂቃ ላይ የድሬደዋ ተከላካዮችን መዘናጋትን ተከትሎ አብዱራህማን ሙባረክ አፄዎችን አቻ የምታደርግ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ማግኘት ቢችልም የድሬደዋ ከተማ የልብምት የሆነው ጉዙፉ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ በሚገርም ሁኔታ አድኖበታል፡፡

ጨዋታው በመጀመርያዎቹ 25 ደቂቃ በነበረው ፍጥነት ሳይቀጥል እየቀዘቀዘ ይሉቁንም 30-45 ኛው ደቂቃ ድረስ ጨዋታው ሀይል የተቀላቀለበት አከራካሪ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ ተከትሎ በሚፈጠር ክርክር ጨዋታው እየተቆራረጠ ቀጥሏል፡፡ 44ኛኛው ደቂቃ ላይ በረከት ይስሐቅ በግራ እግሩ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ በጎሉ ጠርዝ ታክኮ ከወጣው ሙከራ ውጪም ሌላ ሙከራ ሳይታይ በድሬዳዋ 1-0 መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ አፄዎቹ በኳስ ቁጥጥር ተሽለው የቀረቡበት የጨዋታ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም የግብ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ውለዋል፡፡  ምናልባትም ተጠቃሽ ሊሆን የሚችለው የጎል ሙከራ የመጨረሻው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሙሉቀን ሙሉቀን ታሪኩ ያመከነው ኳስ ብቻ ነው፡፡
በአንፃሩ ባለ ሜዳዎቹ ድሬዳዋዎች ውጤት ለማስጠበቅ በሚመስል ሁኔታ ሰአት የማባከን እና የጥንቃቄ አጨዋወትን በመከተል አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው በመጀመርያው ደቂቃ በተቆጠረችው ብቸኛ ጎል በድሬደዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ለድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት ስራ በዝቶባቸው የዋሉት ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል እና ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ ያሰዩት ግሩም እንቅስቃሴ የብዙዎችን አድናቆት አስችሯቸዋል። ድሉን ተከትሎም በስታድዮሙ የተገኙት የድሬደዋ ከተማ ደጋፊዎች ደስታቸውን ሲገልፁ አምሽተዋል፡፡

ውጤቱ ድሬዳዋ ከተማ ነጥቡን 15 በማድረስ ደረጃውም ወደ 11ኛ ከፍ እንዲያደርግ ሲረዳው በተከታታይ ጨዋታዎች ውጤት የራቀው ፋሲል ከተማ በ20 ነጥቦች ወደ 7ኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *