የጨዋታ ሪፖርት | ወልድያ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታድየም ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያስተናገደው ወልድያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡

የኤሌክትሪኮች መጠነኛ የጨዋታ ብልጫ እና የወልድያዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በተስተዋሉበት የመጀመሪያው አጋማሽ ገና በመጀመሪያው ደቂቃ የወልድያ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል የፈጠሩት መዘናጋት ዳዊት እስጢፋኖስን ከግብ ጠባቂው ቢሌንጌ ጋር ቢያገናኝም ቢሌንጌ በሚገርም ብቃት ኳሱን ያዳነበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡

በ9ኛው ደቂቃ ያሬድ ሀሰን ከቢኒያም ዳርሰማ በጥሩ ሁኔታ የተቀበለውን ኳስ አንድ ተከላካይ አልፎ ሞክሮት በረኛው ሲይዝበት ከ1 ደቂቃ በኋላ ያሬድ ሀሰን ወደ ሳጥኑ የላካትን ኳስ አንዱአለም ንጉሴ በግንባሩ በመግጨት ወልድያን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸው  ጎል ለማግኘት ሙከራዎችነ ማድረግ ችለው ነበር፡፡ በ16ኛው ደቂቃ ብሩክ አየለ ከሳጥኑ ውጭ የሞከረው ኳስ በግቡ ቋሚ በኩል የወጣበት እንዲሁም በ39 ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ወልድያ የግብ ክልል ከተጠጉ በኋላ የተሻማውን ኳስ ቢሌንጌ ሲመልሰው ከቦክስ ውጭ ሞክረው የወጣባቸው ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ። በወልድያም በኩል ዮሃንስ ሃይሉ በ29ኛው ደቂቃ በግራ በኩል ወደ ጎል የላከው እና ማንም ሳያገኘው የወጣው ኳስ ወርቃማ የጎል እድል ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወስደው የተጫወቱት ኤሌክትሪኮች አቻነት ጎል ለማስቆጠር ተጭነው ተጫውተዋል።  ወልድያዎች በበኩላቸው በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውሏል፡፡ በ60ኛው ደቂቃ ሙሉጌታ ረጋሳ የሞከረው ኳስም ለዚህ እንደ ማሳያ ነበር፡፡

በ72ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ወልድያ የግዕ ክልል የተጠጉት ኤሌክትሪኮች በፍጹም ገብረማርያም አማካኝነት ጎል አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል፡፡

በ82 ደቂቃ የኤሌክትሪኩ ዳዊት እስጢፋኖስ እና የወልድያው ዳንኤል ደምሴ በጨዋታ ሂደት ዳዊት ዳንኤልን ጎትቶ በመያዙ ዳኛው በፊሽካ ካስቆሙ ቡኀላ ዳዊትን ሆን ብለህ በክርንህ ተማተሀል በሚል በዳንኤል ደምሴ ላይ የቀይ ካርድ መዘውበታል። በዚህም የተነሳ በተፈጠረ ጭቅጭቅ ጨዋታው ለ5 ደ ያህል ለመቋረጥ ተገዶ ነበር፡፡ ይህ ቀይ ካርድ ለዳንኤል ደምሴ በውድድር ዘመኑ 2ኛ የቀይ ካርድ ሆኖ ተመዝግቦበታል፡፡

በቀሩት ደቁቃዎች ሁለቱም ቡድኖች አሸንፈው ለመውጣት ጥረት ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ በ89ኛው ደቂቃ በግራ መስመር በኩል ኤሌክትሪኮች የሞከሩት አደገኛ ኳስ ቢሌንጌ ሲያወጣው በ90ኛው ደቂቃ አንዱአለም ንጉሴ የሞከረው አደገኛ ኳስ በሱሌይማን አቡ ጥረት ጎል ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ጨዋታውም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply