ፕሪምየር ሊግ | ሲዳማ ቡና ሲያሸንፍ አዳማ እና ወላይታ ድቻ በሜዳቸው ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት 2ኛ ቀን 7 ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ሲዳማ ቡና ሲያሸንፍ አዳማ እና ወላይታ ድቻ ደግሞ በሜዳቸው ነጥብ ጥለዋል፡፡

ይርጋለም ላይ ደደቢትን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 2-0 በማሸነፍ ከመሪዎቹ ያለውን ልዩነት አጥብቧል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ ደደቢት የእንቅስቃሴ ብልጫ የነበረው ቢሆንም የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም፡፡ ይልቁንም በመልሶ ማጥቃት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሲዳማዎች ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው 8 ደቂቃ ብቸቻ ነበር፡፡ ናይጄርያዊው አጥቂ ላኪ በሪለዱም ሳኒ ከአዲስ ግደይ የተሸጋገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ ደደቢቶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችላቸው ሙከራዎችን በጌታነህ ከበደ እና ኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ቢሞክሩም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ በሲዳማ ቡና 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተቀዛቀዘ መልክ ሲኖረው ጥቂት የግብ ሙከራዎች ብቻ ተስተናግደዋል፡፡

በ84ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በደደቢት የፍጹም ቅጣት ምት ክልል በአክሊሉ አየነው በመጠለፉ የተሰጠውን አወዛጋቢ ፍጹም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ ግደይ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን ለ2-0 ድል አብቅቶታል፡፡

ፌዴራል ዳኛ ደረጄ ገብሬ የሰጡት የፍጹም ቅጣት ምት በደደቢት በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ ለረጅም ደቂቃዎች ጭቅጭቅ አስከትሏል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ በሜዳው በደደቢት ተሸንፎ የማያውቀው ሲዳማ ቡና ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን ልዩነት ወደ 2 ሲያጠብ ከደደቢት ጋር በነጥብ ለመስተካከል ችሏል፡፡

ሲጠበቅ የነበረው የዳንጉዛ ደርቢ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ወላይታ ድቻ በጨዋታው ብልጫ የነበረው ቢሆንም በጥልቀት የተከላከለው የአርባምንጭ የተከላካይ ክፍልን መስበር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ጨዋታው ቁጥሩ እጅግ በርካታ በሆኑ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ደምቆ ተደርጓል፡፡

አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ከመከላከያ ያለ ግብ አቻ ተለያይቶ የሊጉን መሪነት የመረከብ እድሉን አምክኗል፡፡ በጨዋታው አዳማ ከተማ በሚካእል ፣ ዳዋ እና ፋሲካ አስፋው አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም በጨዋታው ድንቅ የነበረው አቤል ማሞ ጎል ከመሆን ታድጓቸዋል፡፡

Leave a Reply