ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 አዲስ አበባ ከተማ | የአሰልጣኞች አስተያየት

የ2008 ቻምፒዮኖቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአበባ ቢቂላ ስታዲየም አዲስ አዳጊውን አዲስ አበባ ከተማን አስተናግደው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡ 1-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ሲያስጠብቅ አዲስ አበባ ከተማ የሊጉ ግርጌ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡

የሁለቱ ቡድን  አሰልጣኞች ከጨዋታው በኋላ የሰጡት አስተያየት ይህንን ይመስላል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ማርት ኑይ

ስለጨዋታው

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ለማስቆጠር ሁሉንም ነገር አድርጓል፡፡ ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ሶስት ደቂቃዎች ብቻ ላይ ነው ስኬታማ ሆነን ግብ ማስቆጠር የቻልነው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ስህተት ሰርተናል፡፡ ቡድኑ መጥፎ ጨዋታ አይጫወትም በአንድ ተጫዋች ተራ ስህተት 1-0 እንድንሆን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ወደ ጨዋታው ለመመለስ እና ግብ ለማስቆጠር ሁሉንም ነገር አድርገናል፡፡ እንደ እድል ሆኖ ስህተቱን የሰራው ተጫዋች የአቻነት ግብ አስቆጥሮልናል፡፡”

“እኔ ስለግቡ መዳኘት አልችልም፡፡ እዚህ በካፍ እና ኢ.እ.ፌ. ብቁ የሆኑ ዳኞች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ በዳኝነት ላይ አስተያየት አልሰጥም፡፡”

የአዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ

ስለጨዋታው

“በአጠቃላይ በዛሬ ውሏችን ደህና ነበርን ብዬ ነው ማስበው፡፡ በተወሰነ ደረጃ በመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በጊዮርስ በኩል የተወሰነ ጫና ነበር፡፡ ግን በኃይል የዘለቀ አይደለም፡፡ በእኛም በኩል የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ጥረት አድርገናል፡፡ ጠዋት በነበረው ፕሪማች ፕሮግራም ላይ በተለይ ዳኝነትን በተመለከተ በአፅኖት ለመናገር ሞክረናል፡፡ እኛ ዛሬ አቻ ሳይሆን ማሸነፍ የምንችልበትን እድል አጥተናል፡፡ እንደእኔ እይታ ከተሳሳትኩ ልታረም እችላለው የመጀመሪያው ግብ ከጨዋታ ውጪ ነው ብዬ ነው ማስበው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ያገኘነውን የፍፁም ቅጣት ምትም ቢሆን ዳኛ እዛ ላይ ያየውን ነገር መተርጎም ነው ያለበት፡፡ ስለዳኛው ብዙ መናገር አልችልም፡፡ በተመሳሳይ አርባምንጭ ላይም ይሄ ዳኛ ለአርባምንጭ የሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት መጀመሪያም ተናግረናል፡፡ በተለይ በሁለተኛው ዙር የውድድር ጫናዎች እየበዙ ሲሄድ ዳኝነቱም መጥራት አለበት፡፡”

ተጨማሪ ግብ አለማስቆጠር

“ይህ የጥራት ጉዳይ ነው፡፡ ለማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች ለማስኬድ ሞክረናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ነቅዬ እሄዳለው ስትልም አዳጋ ስላለው ጊዮርጊስም ያሉት የበሰሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ይህንን ክፍተት ተጠቅመው በቶሎ ቢያገቡብን አድጋ ነው፡፡ ይህንን ግብ አስጠብቀን ረጅም ሰዓት መጓዛችን ጥሩ ነገር ነው፡፡ የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ነው እነሱ ያቺን ግብ ያገኙት፡፡ ከመጀመሪያውም እያጠቃን ብንሄድ ክፍተቶች ይኖራሉ ይህማ አደጋ ነው፡፡ ስለዚህ የመረጥነው ነገር ለእኛ ጥሩ ነው ብዬ አስባለው፡፡ አንድ ነጥብም ያገኘንበት ዋናው ነገር ከእዛ አኳያ ነው፡፡”

Leave a Reply