አሰልጣኙ መጥተዋል

የመምጫቸው ቀን ረዝሞ ልብ ሲያንጠለጥሉ የቆዩት አሰልጣኝ ጎራን ስቲቫኖቪች በመቸረሻም ዛሬ ረፋዱ ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ ጎራን ለድርድር የመጡት ህጋዊ የፊፋ ወኪላቸውን ይዘው ሲሆን አዲሱ የፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ ተቀብለዋቸዋል፡፡

ሰርቢዊው የ47 አመት ጎልማሳ ነገ ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በደሞዝ ፣ ጥቅማ ጥቅምና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ድርድር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ድርድሩ በተለይ በደሞዙ መጠን ዙርያ ከፌዴሬሽኑ የሚወጡት ጭምጭምታዎች እና የጎራን ፍላጎት ላይጣጣም ስለሚችል ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡

ፌዴሬሽኑ ለአሰልጣኙ ለመክፈል ያቀደው ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ቢሆንም በ2012 በጋና አሰልጣኝነታቸው በወር 35 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ይከፈላቸው የነበረው ጎራን ከ2 አመታት በኋላ በሌላዋ አፍሪካዊት ሃገር መጠኑ በእጅጉ ባነሰ ደሞዝ ለመስራት ይስማማሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡

የአሰልጣኙ እና የፌዴሬሽኑ ድርድር በስኬት ከተጠናቀቀ የቀድሞው የዩጎዝላቪያ ሪፑብሊክ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የነበሩት የ47 አመቱ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ በይፋ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ይሆናሉ፡፡ ይህ ካልተሳካ ደግሞ እንደ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ገለፃ ከፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ጋር ድርድር ያደርጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለውጪ አሰልጣኝ የሚሆን በቂ ገንዘብ በካዝናው መኖሩን ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ